ዳያስፖራው በሚያደርገው የልማት እንቅስቃሴ አርአያነት ያለው ተግባር እንዲያከናውን ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራው በሚያደርገው የልማት እንቅስቃሴ አርአያነት ያለው ተግባር እንዲያከናውን ተጠየቀ
አዲስ አበባ መስከረም 20/2011 ዳያስፖራው በሚያደርገው የልማት እንቅስቃሴ አርአያነት ያለው ተግባር እንዲያከናውን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ጠየቀ። ማህበሩ ከአቤጋስ ማኔጅመንትና ጋር በመተባበር "ዳያስፖራው ለልማት" በሚል አገር አቀፍ የውይይት መድረክ ትናንት አካሂዷል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ ቱሪስት ስራ ድርጅት ዳያስፖራው መሰማራት የሚችልባቸውን የኢንቨስትመንት እድሎችና ማበረታቻዎች በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል። በዚህ ጊዜ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አብርሃም ስዩም እንደገለጹት፤ ዳያስፖራው በሚሰማራባቸው የኢንቨስትመንት መስኮች አርአያ የሆኑ ተግባራትን ማከናወን ይጠበቅበታል። ዲያስፖራው በሚኖርበት አገር ማንነቱ ተከብሮ፣ መብቱ ተጠብቆና በነጻነት መንቀሳቀስ እንደሚችል ጠቅሰው በኢትዮጵያም እነዚህ መብቶቹ እንዲጠበቁ ለማስቻል መስራት ተገቢነት እንዳለው ጠቁመዋል። በተለይ በኢትዮጵያ ድህነትን ለማሸነፍ በሚደረገው ጥረት መከፋፈልን በማስወገድ፣ ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ በመፍታትና ልዩነትን በማስተናገድ የአገሪቷ ኢንቨስትመንት እንዲጎለብት መንቀሳቀስ ያስፈልጋል። ለዚህም ማህበሩ ዳያስፖራውን ተቀብሎ የማስተናገድ፣ አስፈላጊውን መረጃ የመስጠትና በፍጥነት ወደ ልማት እንዲገባ የሚያደርገውን ድጋፍና እገዛ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ተካ ገብረየሱስ በበኩላቸው ዳያስፖራው ህጋዊ የኢንቨስትመንት ስርዓቱን ጠብቆ አገሪቷ ቅድሚያ በምትሰጠው የማምረቻ መስክ ቢሰማራ ውጤታማ መሆን እንደሚችል አስገንዝበዋል። ዳያስፖራው በግብርና ምርት ማቀነባበር፣ በመድሃኒት አቅርቦትና ምርት፣ በጨርቃ ጨርቅ፣ በቆዳና ሌጦ፣ በአበባና ፍራፍሬ፣ በቱሪዝምና በኃይል አቅርቦት ዘርፎች ቢሰማራ መንግስት ከዘጠኝ እስከ 14 ዓመት የሚቆይ ማበረታቻ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል። ዳያስፖራው በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ቅድሚያ የሚያገኝባቸውን እድሎችን በመጠቀም ለራሱና ለአገሩ አስተዋጾኦ እንዲያበረክት ጥሪ አስተላልፈዋል። ባለፉት ሶስት ዓመታት በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት በኢንቨስትመት ቦታዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ምክትል ኮሚሽነሩ አስታውሰው በቀጣይ መሰል ተግባራት እንዳይፈጸሙ በጥናት ላይ የተመሰረተ መፍትሄ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የውጭ ንግድ ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ በየነ እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ተወዳዳሪ ለመሆን አለም አቀፍ ህግጋትን መሰረት ያደረጉ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። ይህም ዳያስፖራው በአገሩ በንግድ እንቅሰቃሴ የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለመቅረፍ ያስችላል ብለዋል። መንግስት ዳያስፖራው በህግጋቶቹ ላይ ግንዛቤ እንዲኖረው፣ ህግን እንዲያከብርና እንዲያስከብር፣ ለአገሩ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያመጣ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሥራ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ሌንሳ መኮንን በአገሪቱ እምቅ የቱሪዝም አቅም እንዳለ ተናግረው ዳያስፖራው ስትራቴጂካዊ በሆነና ሥርዓት ባለው ሁኔታ ይህን አቅም እንዲጠቀም ጠይቀዋል። ዳያስፖራው በኖረባቸው አገሮች ያሉትን የተለያዩ የቱሪዝም ልምድና ተሞክሮ አገር ውስጥ ቢጠቀማቸው ድርጅቱ አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አክለዋል። የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት ለመሰማራት ያሉትን እድሎች፣ አማራጮች፣ ህግጋቶችና አሰራሮች በተመለከተ ወቅታዊ መረጃ መስጠት ተገቢ እንደሆነ በመግለጽ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ወይዘሮ ሳራ አህመድ የተባሉ አስተያየት ሰጪ በአገሪቷ ንግድና ኢንቨስትመን እንዲስፋፋ መንግስት ለሰላም፣ ጸጥታና የህግ የበላይነት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ጠይቀዋል። ሌላው አስተያየት ሰጪ ሐጂ ሙጃተና አሊ ደግሞ መንግስት ለአውሮፓና ለአሜሪካ ዳያስፖራዎች የሚሰጠውን ትኩረት በአረብ አገሮች ለሚገኙ ዜጎች መስጠት ይኖርበታል ሲሉ ገልጸዋል። መንግስት ንግድና ኢንቨስትመንትን የሚመለከቱ ህጎች ሲያሻሽልና ሲቀይር ችግር እንዳያስከትሉ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ አቶ የሻው ለማ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ናቸው።