ነቀፌታን በድል ተሻግሮ ለቀጣይ የውድድሩ አዘጋጆች ትልቅ የቤት ስራ የሰጠ የዓለም ዋንጫ - ኢዜአ አማርኛ
ነቀፌታን በድል ተሻግሮ ለቀጣይ የውድድሩ አዘጋጆች ትልቅ የቤት ስራ የሰጠ የዓለም ዋንጫ
የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ከ90 ዓመታት በላይ እድሜ ያስቆጠረ ቢሆንም በተለይ የአፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ አገራት የተሰጣቸው የአዘጋጅነት ዕድል እጅግ አናሳ ነው።
22ኛው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ የአዘጋጅነት ሚና ግን በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥም ቢሆን ለኳታር ተሰጥቷል።
የዓለም ዋንጫ ማዘጋጀት ከእግር ኳስም በላይ ነው የሚባልለትን ይህን ውድድር ስታዘጋጅ ግን በመገናኛ ብዙሃን በኩል የተከፈተባት ዘመቻ ቀላል አልነበረም።
ኳታር የውድድሩን አዘጋጅነት እድል ያገኘችው በእጅ መንሻ ነው ከሚለው ሀሳብ ጀምሮ ጫናው እጅጉን ከፍ ያለ ነበር።
ከዚህ በላይ ጎልቶ ይነሳ የነበረው የዓለም ዋንጫ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ወደ ኳታር ያመሩ የውጭ አገር ሰራተኞች ለከፍተኛ የሰብአዊ መብት አያያዝ ችግር ተጋልጠዋል የሚል ነበር።
በእርግጥ በኳታር ለውድድሩ ዝግጅት ስታዲየሞች ጨምሮ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት ከፓኪስታን፣ ህንድ፣ ባንግላዲሽ፣ ኔፓል፣ ስሪላንካ እና ሌሎች አገሮች ከመጡ ሰራተኞች ውስጥ በጥንቃቄ ጉድለት በመቶዎች መሞታቸውን ዘግይታም ቢሆን ማመኗን መረጃዎች አመላክተዋል። አንዳንዶች ግን የሟቾች ቁጥር በሺዎች የሚቆጠር መሆኑን ይገልጻሉ።
ኳታር በብዙ ትችቶች ታጅባ፣ ነቀፌታዎችን ችላ አለፍ ሲልም የእግር ኳሱ መሪዎች ሳይቀሩ የአዘጋጅነት እድል ለኳታር መሰጠቱን እንደ ስህተት መጥቀሳቸውን ተቋቁማ ትኩረቷን ዝግጅቱ ላይ ማድረግን መርጣለች።
ውድድሩ ሲቃረብም ወደ ኳታር የሚሄዱ የእግር ኳስ ደጋፊዎች፣ ተጫዋቾች፣ እና ሌሎችም አካላት የግብረሰዶማውያን ምልክት ማስተዋወቅም ሆነ አርማቸውን መጠቀም እንዲሁም የአልኮል መጠጥ በፈለጉበት ቦታና ሰዓት መጠጣት ሊፈቀደላቸው ይገባል የሚል ሌላ ዘመቻ ጎልቶ መሰማት ጀመረ።
በአንድ በኩል የግለሰቦችን ነጻነት ለምትጋፋ ሀገር የአስተናጋጅነት እድል መሰጠቱ በእጅ መንሻ የተገኘ ነው የሚሉ ሀሳቦች ተበራከቱ። ዕድሉ ከኳታር እንዲነጠቅም ብዙ ተሞከረ፤ ግን አልተሳካም።
የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በዶሃ የውድድሩ መክፈቻ ጋዜጣዊ መግለጫ በተሰጠበት ወቅት በሰብአዊ መብት አያያዝና ሌሎች ጉዳዮች ኳታርን ለሚከሱ አካላት ጠንከር ያለ ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል።
ኢንፋንቲኖ ከፍፃሜው ጨዋታ ቀደም ብሎ በሰጡት መግለጫም የኳታር 2022 የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ የምንጊዜም ምርጡ ውድድር ነበር ሲሉ አሞካሽተውታል።
በእርግጥም የኳታሩ የዓለም ዋንጫ ከተጠበቀው በላይ ግሩም ሆኖ መጠናቀቁን በርካቶች መስክረዋል። ከእግር ኳሱ ቤተሰቦች ልብ ውስጥ በማይወጡ አስደማሚ ክንውኖች የታጀበም ሆኖ አልፏል።
ኳታር ወሬውና ጫጫታው ሳይበግራት ስኬታማ ውድድር ማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን ገጽታዋን ለመገንባትም ውድድሩን በሚገባ ተጠቅማበታለች።
በተፈጥሮ ጋዝ ክምችት በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት አገራት አንዷ የሆነችው ኳታር በተለይ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዓለምን አስደምማለች።
በረሃማ ቦታም ከተሰራበት መልማት እንደሚችል ቅንጡና ዘመናዊ ሆቴሎችን ጨምሮ አስደማሚ መሰረተ ልማቶች ሰርታ አሳይታለች።
ኳታር እስካሁን የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ካዘጋጁት ሀገራት በጣም ትንሿ ሀገር ስትሆን እስካሁን ከተዘጋጁ የዓለም ዋንጫዎች የምንጊዜም ውድ የተባለውን ወደ 220 ቢሊዮን ዶላር ወጪ በማውጣት በሰራችው ስራ የተቺዎቿን አፍ አዘግታለች።
ስምንት ስታዲየሞችን ለውድድሩ ያሰናዳች ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ሰባቱ አዲስ ናቸው። ከነዚህም ስታዲየሞች መካከል ስታዲየም 974 ይገኝበታል።
ይህ ስታዲየም ስያሜያውን ያገኘው ድጋሚ ጥቅም ላይ ከዋሉ 974 የመርከብ ዕቃ ማጓጓዣ ኮንቴነሮች የተሰራ በመሆኑ ነው።
በተጨማሪም የስታዲየሙ ስያሜ የኳታር የስልክ መለያ ቁጥር የሚጀመረው +974 ከመሆኑ ጋር ይያያዛል። የስታዲየሙ ንድፈ ሀሳብ የተዘጋጀው ‘ፌንዊክ ኢሪባረን አርክቴክት’ የተሰኘ የሕንጻ ዲዛይን ድርጅት ነው። የተወሰኑት ኮንቴነሮች የፋይናንስ አገልግሎት መስጫዎችና መኪና ማቆሚያዎች አሉት።
ይህም ስታዲየም 974ን በፊፋ ዓለም ዋንጫ ታሪክ የመጀመሪያ ጊዜያዊ ስታዲየም ያደርገዋል። በቀላሉ የሚነቃቀለውን ስታዲየም መልሶ በድጋሚ መገጣጠም ይቻላል።
የኳታሩ የዓለም ዋንጫ አዳዲስ ነገሮችን በማስመልከት ብዙ አይረሴ ትዝታዎች ጥሎ አልፏል።
ከእነዚህ አዳዲስና አይረሴ የኳታር የዓለም ዋንጫ እውነቶች አንዱ ውድድሩ የተካሄደበት ወቅት ነው። ከዚህ በፊት ውድድሩ በአውሮፓውያን አቆጣጠር በበጋ ወቅት ይደረግ የነበረ ሲሆን የኳታሩ ዓለም ዋንጫ ግን በክረምት የተዘጋጀ የመጀመሪያ ውድድር ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል።
የዓለም ዋንጫ ሴት ዳኞች ለመጀመሪያ ጊዜ በዳኝነት መካፈላቸውም ልዩ ከሚያደርጉት ነገሮች ውስጥ ተጠቃሽ ነው።
በምድብ የመጀመሪያ ጨዋታ ያልተጠበቀ ሽንፈትን በሳውዲ አረቢያ ያስተናገደችው አርጀንቲናን ጨምሮ የዓለማችን ታላላቅ ቡድኖች ሽንፈት ሲገጥማቸው፣ ሞሮኮና ጃፓን አይነት ብዙም ትኩረት ያልተሰጣቸው ቡድኖች ደግሞ አይረሴ ታሪክ ሰርተዋል።
በተለይ አፍሪካ በሞሮኮ ብሄራዊ ቡድን በእግር ኳስ ታላላቅ የሚባሉትን በመጣል ግማሽ ፍጻሜ በመግባት አዲስ ታሪክ የሰራችበት ነበር። ይህም ለሞሮኮ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም አዲስ ታሪክ ሆኖ ተመዝግቧል።
ልብ አንጠልጣይ የነበረው የአርጀቲናና ፈረንሳይ የፍጻሜ ጨዋታ የማይረሱ ትዝታዎች ጥሎ አልፏል።
በጥቅሉ የኳታር የዓለም ዋንጫ በከፍታና በስኬት መጠናቀቁ በቀጣይ ውድድሩን በጥምረት የሚያዘጋጁ አገራት ከወዲሁ በስፋት መዘጋጀት እንዳለባቸው የቤት ስራ የሰጠ አስደማሚ ውድድር ሆኖ ፍጻሜውን አግኝቷል።