ቀጥታ፡

የሕዳሴ ግድብ የቀጣናው አገራትን በማስተሳሰር ለምጣኔ ኃብት እድገትና ዘላቂ ሰላም ከፍተኛ ሚና ያበረክታል- ላውረንስ ፍሪማን

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 11/2015 ታላቁ የህዳሴ ግድብ የቀጣናው አገራትን በማስተሳሰር ለምጣኔ ኃብት እድገትና ዘላቂ ሰላም ከፍተኛ ሚና እንደሚያበረክት አሜሪካዊው የፖለቲካል-ኢኮኖሚ ተንታኝ ላውረንስ ፍሪማን ገለጹ።

አሜሪካዊው የፖለቲካል-ኢኮኖሚ ተንታኙ ላውረንስ ፍሪማን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደትን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

ጉብኝታቸውን ተከትሎ በሰጡት አስተያየት፤ ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ በራሷ አቅም ማከናወኗ ለአፍሪካውያን ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ለግድቡ ግንባታ እያደረጉት ያለው ተሳትፎ የሚደነቅ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ላይ ጀቡቲን ጨምሮ ለጎረቤቶቿ ኃይል እያቀረበች መሆኑን ጠቅሰው፤ የህዳሴ ግድብ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ ይህን ትስስር ይበልጥ እንደሚያጠናክረው አብራርተዋል፡፡

የግድቡን ግንባታ ሂደት በመጎብኘታቸው ትልቅ ደስታ እንደፈጠረላቸው ገልጸው፤ ግድቡ ሲጠናቀቅ ለቀጣናው ምጣኔ ኃብታዊ ልማትና ለዘላቂ ሰላም አበርክቶው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ግድቡ በአፍሪካ የሃይል አቅርቦት ለማስፋት ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ አገራቸው አሜሪካን ጨምሮ ምእራባውያን ይህንን የኢትዮጵያ ጥረት ሊያደንቁት ብሎም ሊደግፉት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

አፍሪካ በርካታ የኃይል መሰረተ-ልማት ያስፈልጋታል ያሉት ተንታኙ፤ የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ ለአፍሪካ ቀንድ አዎንታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የግድቡ ግንባታ ወደ ታችኛው የተፋሰስ አገራት በሚፈሰው የውኃ መጠን ላይ ጉልህ ተዕጽኖ ሊኖረው እንደማይችል ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የታችኛው ተፋሰስ አገራትን ከግምት በማስገባት ዓመቱን ሙሉ የውሃ ፍሰቱ ሳይቋረጥ የግድቡን ግንባታ እያከናወነች መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የታችኛው ተፋሰስ አገራት ግድቡን በተመለከተ ቅሬታ ሊያነሱበት የሚያስችል ምክንያት ሊኖራቸው እንደማይገባ ነው የተናገሩት፡፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብ እንደ አድዋ ሁሉ የኢትዮጵያውያን የጋራ ድል መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡

ኢትዮጵያ በቅርቡ የግድቡን ሦስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት ማጠናቀቋ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም