ቀጥታ፡

ቅርሶችን በማልማት ማህበረሰቡን የሚጠቅሙ አሰራሮችን እንተገብራለን - የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን

ሀረሪ (ኢዜአ) ታህሳስ 11/2015 ቅርሶችን በማልት የማህበረሰብ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ አሰራሮችን ለመተግር በትኩረት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

ባለስልጣኑ በታሪካዊው የጀጎል ግንብ ውስጥ ሞዴል የሆነ መንደርን መፍጠር በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ በሀረሪ ክልል ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ መድረክ አካሂዷል፡፡

በኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን የቅርስ ልማት ባለሞያ አቶ ሚኪያስ ቲዎድሮስ እንደገለፁት ቅርሶችን ለመጠበቅ መጠገን እና ማቆየት ብቻ በቂ አይደለም፡፡

ቅርሱን በተገቢው መንገድ ለመጠበቅ እና ለመንከባከብ እንዲቻል የአካባቢውን ነዋሪዎች ቅርሱ ከሚያመነጨው ገቢ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ማህበረሰቡን በማሳተፍ በውጭ አገራት የሚከናወኑ የቅርስ ጥበቃ አሰራሮችን ተሞክሮ በመውሰድ   በአገሪቱ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ባለስልጣኑ በጀጎል ውስጥ "ሞዴል የሆነ መንደር" ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሞዴል መንደሩ ተግባራዊ መሆን ጀጎል ፅዱና ለኑሮ አመቺ እና ለማህበረሰቡ የገቢ ምንጭ የሚያስገኝ ከመሆን ባለፈ  ከፍሳሽ ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን ይቀርፋል ብለዋል።

አቶ ሚኪያስ አያይዘውም ቅርሶችን ይበልጥ ትርጉም እንዲያገኙ የማይዳሰሱ የማህበረሰቡን ወግ እና ባህላዊ ልማዶች ከቅርሱ ጋር በማዋሃድ ጎብኚው እንዲመለከታቸው ለማድረግ ባለስልጣኑ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጻዋል፡፡

የሀረሪ ክልል ባህል ቅርስ እና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ነቢል በክሪ በበኩላቸው  የአለም ቅርስ የሆነውን ታሪካዊውን የጀጎል ግንብ ለቱሪስት ምቹ በማድረግ ማህበረሰቡን ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ  እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሞዴል መንደሩ የቱሪስት ፍሰቱን ከማሳደግ አንፃርም ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በሀረሪ ክልል አብደላ ሸሪፍ የግል ሙዚየም መስራች ዶክተር አብዱላሂ አሊ ሸሪፍ በበኩላቸው ከተማዋ ከ1ሺ አመት በላይ ያስቆጠረች እንደመሆኗ አስፈላጊው እንክብካቤ አልተደረገላትም ያሉ ሲሆን ፕሮጀክቱ ለቅርሱ እንክብካቤ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ቢለዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ተግባራዊነት ደግሞ የሑሉንም ማህበረሰብ ትብብር እና የመንግስትን ቁርጠኝነት የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ቱሪስቶች ወደ ክልሉ በሚመጡበት ጊዜ ቅርሱን ብቻ ሳይሆን የማህበረሰቡን ባህላዊ እሴቶች እና የእለት ተእለት ኑሮ መመልከት እንዲችሉ መደረግ አለበት ብለዋል፡፡

ቱሪስቶችን በከተማው እንዲቆዩ በማስቻል ማህበረሰቡን የኢኮኖሚ ተጠቀሚ በማድረግ ማህበረሰቡ ቅርሱን እንዲንከባከብ ለማድረግ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተገነባው የጀጎል ግንብ በውስጡ አምስቱ በሮች፣ ረጅም እድሜን ያስቆጠሩ መስጊዶች፣ የፈረንሳዊው ጸሃፊ የአርተር ራንቡ መኖርያ ቤት፣ ሙዚየሞች፣ የሀረሪ ባህላዊ ቤቶች፣ የጅብ ምገባ ትርዒት ማሳያ ስፍራ እና ሌሎች  ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ጥንታዊ የመስህብ ስፍራዎች ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም