ከመልሶ ማቋቋም ተግባራት ባሻገር ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ግንባታ የበኩላችንን ድጋፍ እናደርጋለን-የመንግሥታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም - ኢዜአ አማርኛ
ከመልሶ ማቋቋም ተግባራት ባሻገር ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ግንባታ የበኩላችንን ድጋፍ እናደርጋለን-የመንግሥታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 11 /2015 የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (ዩ ኤን ዲፒ) በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለማቋቋም ከሚከናወኑ ተግባራት ባሻገር ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተወካይ ቱሩሃን ሳልህ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሰላም ስምምነቱ ሀገሪቷ በሙሉ አቅሟ ፊቷን ወደ ልማት እንድታዞር ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡
ይህም ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ኢትዮጵያ በልማት መስክ የጀመረችውን የለውጥ ሥራ እውን እንድታደርግ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
በተለይም በሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም መንግሥት በጦርነቱ የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ለሚያከናውናቸው ሥራዎች ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
"ያለ ሰላም ልማትን ማረጋገጥ አይቻልም"ያሉት ተወካዩ፤ ከዚህ አኳያ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተፈጠረው ጦርነት በሰላም ለመቋጨት ስምምነት ላይ መደረሱ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን የሰላም ስምምነቱን እንደ በጎ እድል በመጠቀም አገራቸውን ወደ ከፍታ የሚወስዱበት ጊዜው አሁን መሆኑንም አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም መንግሥት የተቋማት አቅምን ለመገንባት እያከናወነ ያለውን ሥራ እንደሚደግፍም ጠቁመዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ በተለያዩ አገራት ያሉ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመር ገቢራዊ እንዲሆኑ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡