ቀጥታ፡

ወረርሽኝ ቢከሰት በብቃት መመከት እንዲቻል የጤና ተቋማት ተገቢውን መረጃ በፍጥነት እንዲያደርሱ ተጠየቀ

ሚዛን አማን (ኢዜአ) ታህሳስ 11 ቀን 2015 ወረርሽኝ ቢከሰት በብቃት መመከት እንዲቻል የጤና ተቋማት ተገቢውን መረጃ በፍጥነት እንዲያደርሱ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጠየቀ።

ኢንስቲትዩቱ ሀገር አቀፍ የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ፎረም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሚዛን አማን ከተማ እያካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ እንዳሉት፤ ኮቪድ 19ን ጨምሮ የተለያዩ ወረርሽኞች የከፋ ጉዳት እንዳያስከትሉ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር ውጤታማ ስራ እየተሰራ ይገኛል።

ወረርሽኝን በመመከት ረገድ የጤና ተቋማት የላቀ ሚና እንዳላቸው ገልጸው፤ በሀገራችን ውስጥ ባሉ የተለያዩ ክልሎች የሚከሰቱ ወረርሽኞችን በብቃት መመከት እንዲቻል የጤና ተቋማት በምርመራ ልየታ ወቅት ተገቢውን መረጃ በፍጥነት እንዲያደርሱም ጠይቀዋል።

በተለያዩ ሀገራት የተከሰተው የዝንጆሮ ፈንጣጣ እና የኢቦላ በሽታ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ተገቢው የቁጥጥር ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከአጎራባች ሀገራት በሚያዋስኑ ሁሉም መግቢያና መውጫ በሮች ተገቢው ቅድመ ዝግጅትና ቅኝት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

የመንገደኞች ጤና ልየታ ሥራ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያና በአምስት ዋና ዋና የየብስ መግቢያና መውጫ ኬላዎች ላይ እየተካሄደ እንደሆነም አመልክተዋል።

በተለያየ ምክንያት በህብረተሰቡ ላይ የሚፈጠረውን አዕምሮአዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና የማኅበራዊ ጤና ተጽዕኖዎችን በሚመለከት የጤና ምላሽ ሥራ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በመከናወን ላይ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ በበኩላቸው በክልሉ ተከስቶ የነበረውን ኩፍኝና ሌሎች አደጋዎችን በተቀናጀ የመከላከል ሥራ ፈጥኖ ምላሽ በመስጠት ጉዳት ሳያደርሱ መቀልበስ መቻሉን ተናግረዋል።

የወባ በሽታ በክልሉ ጉዳት እንዳያደርስ ለመከላከል ተገቢ የጤና ምላሽ ለመስጠት ከኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና አጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ክልሉ ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚዋሰን መሆኑን የጠቆሙት አቶ ጸጋዬ፤ የድንበር አካባቢ ጤናን በማጠናከር ረገድ ተገቢው ትኩረትና እገዛ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ያለው ሀገር አቀፍ የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ፎረም መድረክ እስከ ነገ ይቀጥላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም