የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ከባህረ-ሰላጤው ሀገራት ጋር ያለውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር እያሳደገው እንደሚገኝ ተገለጸ

2186

አዲስ አበባ ታኅሳስ 11/2015 (ኢዜአ) አህጉራዊው የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና አፍሪካ ከባህረ-ሰላጤው ሀገራት ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነትና ኢኮኖሚያዊ ትስስር እያሳደገው እንደሚገኝ ተመላከተ።

የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ከአፍሪካ ጋር ያላት የንግድ ትስስር ከባህረ-ሰላጤው ሃገራት መካከል በቀዳሚነት እንደሚጠቀስም ተገልጿል።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዊሊያም ስቴንሀውስ ከሲ ጂ ቲ ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ በተለይም ዱባይ የአፍሪካን ንግድና ኢንቨስትመንት በተመለከተ ዋና ማዕከል ሆናለች ብለዋል።

በዱባይ 25ሺህ ገደማ የአፍሪካ ካምፓኒዎች እንደሚንቀሳቀሱ አመልክተው ይህም ሀገሪቱ በነጻ የንግድ ቀጣናው የቢዝነስ አጋር እንድትሆን አስችሏታል ነው ያሉት።

አፍሪካውያን ባለሃብቶች የግብይት ማዕከላቸውን በተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ በማድረግና ምርቶችን ወደ አህጉሪቷ በማስገባት በነጻ ንግድ ቀጣናው ስር የገልፍ ሀገራትን ኢኮኖሚያዊ ትስስር እያሳደጉት እንደሚገኝም አስገንዝበዋል።

የዱባይ ወደብ በአፍሪካ ያለው ተደራሽነት መስፋፋትም አፍሪካ ከባህረ ሰላጤው ሀገራት ጋር የሚኖራትን የሎጀስቲክስ አቅርቦት እንደሚያሳድግ በመረጃው ተመላክቷል።

ከገልፍ ሀገራት ጋር ያለው ግንኙነት ከኢኮኖሚያዊ ትስስር ባለፈ ዲፕሎማሲያዊና ወንድማማችነትን መሠረት ያደረገ ነው ያሉት ደግሞ በተባበሩት አረብ ኤሜሬት የኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ ናቸው።

አምባሳደሩ እንደሚሉት ከመካከለኛው ምስራቅ መነሻቸውን ያደረጉ ባለሃብቶችና የቢዝነስ ሰዎች ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጋር በልዩ ልዩ ዘርፎች ግንኙነታቸውን እያጠናከሩ ይገኛል።

እ.አ.አ በጥር 2021 ተግባራዊ መሆን የጀመረው የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ከአጀንዳ 2063 ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና የአህጉሪቱን ወሳኝ የኢኮኖሚ ዘርፎች ማለትም የዲጂታል ንግድ፣ የኢንቨስትመንት ትስስርና ሌሎች የንግድ ግንኙነቶችን በነጻ የንግድ ቀጣና ለማከናውን የተካሄደ ስምምነት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም