ለውጭ ገበያ ከቀረበ የቡና ምርት ከ615 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል-የቡናና ሻይ ባለሥልጣን - ኢዜአ አማርኛ
ለውጭ ገበያ ከቀረበ የቡና ምርት ከ615 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል-የቡናና ሻይ ባለሥልጣን
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታኅሳስ 11/2015 ባለፉት አምስት ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ የቡና ምርት ከ615 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ገለጸ።
የገበያ መዳረሻዎችን በማስፋት ወደ ቻይናና ኢንዶኔዥያ አካባቢዎች ቡና መላክ መቻሉም ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የግብይት ዘርፍ ኃላፊ ሻፊ ዑመር ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ባለፉት አምስት ወራት ለውጭ ገበያ ከ109 ሺህ ቶን በላይ ቀርቧል።
በዚህም የቡና ምርት 615 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ተናግረው፤ ገቢው ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ100 ሚሊየን ዶላር ብልጫ እንዳለው አስታውቀዋል።
የቡና ምርቱ ከተላከባቸው አገራት መካከል ጀርመን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ቤልጂየም፣ አውስትራሊያና ጃፓን እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።
የገበያ መዳረሻዎቹን በማስፋት ዘንድሮ ወደ ቻይና እና ኢንዶኔዥያ ቡና የመላክ ሥራ መጀመሩንና ይህም ለገቢው መጨመር ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።
በዘንድሮ በጀት ዓመት 360 ሺህ ቶን ቡና በመላክ እስከ 2 ቢሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት 302 ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በመላክ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር መገኘቱ የሚታወስ ሲሆን ኢትዮጵያ ባለፉት 4 ዓመታት በዘርፉ ማሻሻያዎች ከፍተኛ የቡና ምርት በመላክ ገቢዋን እያሳደገች እንደምትገኝ ይታወቃል።