በባህር ዳር የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞችን የሚያስታውስ ዓደባባይ ይሰየማል-ዶክተር ይልቃል ከፋለ - ኢዜአ አማርኛ
በባህር ዳር የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞችን የሚያስታውስ ዓደባባይ ይሰየማል-ዶክተር ይልቃል ከፋለ
ባህር ዳር (ኢዜአ) ታህሳስ 11/2015 ለአገር አንድነትና ክብር ለተዋደቁ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች መታሰቢያ ዓደባባይ በባህር ዳር ከተማ እንደሚሰየም የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገለጹ።
የክልሉ መንግስት ለማህበሩ አባላት የሚያደረገው ድጋፍና እንክብካቤ ቀጣይነት ባለው መልኩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዶክተር ይልቃል አረጋግጠዋል።
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ጠቅላላ ጉባኤውን በባህር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው።
የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ አንድነት፣ ሉአላዊነትና ክብር ለዘመናት ተጠብቆ የዘለቀው በአርበኞች ደምና አጥንት እንደሆነ ገልጸዋል።
በየዘመናቱ መስዋዕትነት በመክፈል ኢትዮጵያን ያጸኑ ጀግኖች አርበኞችን ማመስገን ብቻ ሳይሆን ታሪካቸውንም ለትውልድ ማሸጋገር የእዚህ ትውልድ ሃላፊነት መሆኑን ተናግረው የአርበኝነት ታሪክን ለማስቀጠል ትውልዱን እያሰተማሩ ያሉ የማህበሩ አባላትን መደገፍ ይገባል ብለዋል።
የክልሉ መንግስት ለጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባላት እስካሁን ሲያደርገው ከነበረው ድጋፍና እንክብካቤ በተጨማሪ የማህበሩን ሰፊ ፍላጎት ከግምት በማስገባት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንደሚያደርግም ቃል ገብተዋል።
በቅርቡም በባህር ዳር ከተማ ጥንታዊ አርበኞች የፈጸሙትን ተጋድሎ የሚዘክር የመታሰቢያ አደባባይ እንደሚሰየምና ለማህበሩ አቅም ማጠናከሪያ የሚውል ቦታ እንደሚሰጥም አረጋግጠዋል።
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባላትን መብትና ክብር የሚያስጠብቁ ጉዳዮችን በፖሊሲዎች፣ ሕጎችና የልማት ስትራቴጅዎች የማካተት ሥራ መሰራቱን የገለጹት ደግሞ የሴቶች፣ ሕጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ ናቸው።
"ይሁን እንጂ የማህበሩ አባላትን ፍላጎት ለማሟላት የአንድ ወገን እገዛ ብቻ በቂ አይደለም" ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ የማህበሩን አቅም ለማጎልበት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ጠቅላላ ጉባኤው በማህበሩ የ5 ዓመት ስትራቴጅክ ዕቅድ ላይ የዞን አመራሮች ሀሳብን ለማካተትና ለማዳበር ጠቃሚ መሆኑን የገለጹት የማህበሩ ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ ናቸው።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በባህር ዳር ከተማ የመታሰቢያ ዓደባባይ ከመሰየም ጀምሮ ለማህበሩ ለገቡት የድጋፍ ቃልም ልጅ ዳንኤል ጆቴ ምስጋና አቅርበዋል።
በጉባኤው ላይ የክልል እና የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች እንዲሁም የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባላት ተገኝተዋል።