ቀጥታ፡

ምክር ቤቱ በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚውል ሰብዓዊ ድጋፍ ሊያቀርብ ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 11/2015 በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚውል ሰብዓዊ ድጋፍ ሊያቀርብ መሆኑን የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ገለጸ።

በኢትዮጵያ በሰሜኑ አካባቢ የተቀሰቀሰውን ጦርነቱ እንዲያበቃ በፌደራል መንግሥትና በሕወሃት መካከል የሠላም ሥምምነት መደረጉ ይታወሳል።  

ሥምምነቱን ተከትሎ በአካባቢው ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች መንግሥትን ጨምሮ የተለያዩ አካላት የሰብዓዊ ድጋፎች እያደረጉ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት አባላት ድርጅቶች በተናጠል ከሚያደርጉት ድጋፍ ጎን ለጎን በጋራ ድጋፍ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

የምክር ቤቱ የፕላንና ልማት አማካሪ አቶ ሞገስ ደምሴ እንዳሉት፤ ከኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ጋር በመተባበር የምክር ቤቱ አባል ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያቀርቡ ጥሪ ቀርቧል ብለዋል።

"በጥሪው መሰረት በርካታ የምክር ቤቱ አባል ድርጅቶች ምላሽ እየሰጡ ነው" ያሉት አማካሪው እስካሁን በቁሳቁስ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ መገኘቱን አብራርተዋል።

በጥሬ ገንዘብም እንዲሁ ድጋፍ መሰባሰቡን ጠቁመው ምክር ቤቱ በግጭት ጉዳት በደረሰባቸው አማራ፣ አፋርና ትግራይ ክልሎች በተመረጡ ሥፍራዎች ድጋፉን ተደራሽ ይደረጋል ብለዋል።

ድጋፉን ለማቅረብ አራት አገር በቀል ድርጅቶች መመረጣቸውን ጠቁመው ድርጅቶቹም ከኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣንና ከምክር ቤቱ ጋር ሥምምነት መፈረማቸውን ገልጸዋል።        

"ሥምምነት የፈጸሙ ድርጅቶች በሦስቱ ክልሎች በተመረጡ ቦታዎች በቅርቡ የተሰባሰበውን ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ ማድረግ ይጀምራሉ" ነው ያሉት።     

ጦርነቱ ካስከተለው ጉዳት አኳያ አሁን ያዘጋጀነው ድጋፍ በቂ አይደለም፤ በቀጣይም በስፋት ድጋፍ እናደርጋለን ሲሉም ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ ማኅበረሰቡን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችሉ የሥነ-ልቦናና ሌሎች ድጋፎችን ለማቅረብ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም