በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የሶስት ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የውድድር ዓመቱን ሁለተኛ ድል አስመዘገበ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የሶስት ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የውድድር ዓመቱን ሁለተኛ ድል አስመዘገበ
አዲስ አበባ(ኢዜአ) ታህሳስ 11/2015 በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የሶስት ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ መቻልን በማሸነፍ በውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ድሉን አስመዝግቧል።
የዘንድሮው የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም መጀመሩ ይታወቃል።
ቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣መቻል፣ኦሜድላ(በቀድሞ አጠራሩ ፌደራል ፖሊስ)፣ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ፣ባህር ዳር ከነማ፣ፌዴራል ማረሚያ፣ከምባታ ዱራሜ፣ፋሲል ከነማ(በቀድሞ ስያሜው ጎንደር ከተማ)፣ሚዛን አማን ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ በሊጉ የሚሳተፉ ክለቦች ናቸው።
የፕሪሚየር ሊጉ የሁለተኛ ሳምንት መርሐግብር ዛሬ በተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ተጀምሯል።
የሶስት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ መቻልን 35 ለ 31 በመርታት በሊጉ ሁለተኛ ድሉን ማስመዝገብ ችሏል።
ቂርቆስ በመጀመሪያ ጨዋታው ሚዛን አማን ከተማን ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
በሌላ የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ኦሜድላን 44 ለ 35 በማሸነፍ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ድሉን አስመዝግቧል።
ኮልፌ በመጀመሪያ የሊጉ ጨዋታው በመቻል መሸነፉ ይታወሳል።
የፕሪሚየር ሊጉ ሁለተኛ ሳምንት መርሐግብር ነገም ሲቀጥል ፋሲል ከነማ ከባህር ዳር ከነማ ከጠዋቱ 2 ሰአት ከ20 እንዲሁም ሚዛን አማን ከተማ ከፌደራል ማረሚያ ከረፋዱ 3 ሰአት ከ40 ይጫወታሉ።
የፕሪሚየር ሊጉ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ሳምንት ያሉ ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም እንደሚካሄዱ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ሳምንት ያሉ ጨዋታዎች በድሬዳዋ እንደሚደረጉም ገልጿል።
ሰባተኛ የውድድር ዓመቱን የያዘው የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የተጀመረው በ2009 ዓ.ም ነው።
ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ሶስት ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ሲሆን መቻል ሁለት ጊዜ ዋንጫውን አንስቷል። ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ አንድ ጊዜ የወድድሩ አሸናፊ መሆን ችሏል።