የኢትዮጵያ ልማት ባንክና ዩኤንዲፒ በአይቲ ዘርፍ ለተሰማሩ ስራ ፈጣሪዎች የሚውል የ1 ሚሊዮን ዶላር ብድር ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክና ዩኤንዲፒ በአይቲ ዘርፍ ለተሰማሩ ስራ ፈጣሪዎች የሚውል የ1 ሚሊዮን ዶላር ብድር ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሣሥ 11/ 2015 የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እና የመንግስታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ለተሰማሩ ስራ ፈጣሪዎች የሚውል የ1 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱ የብድር ዋስትና ፈንድ ማስተዳደርና ማቅረብ የሚያስችል ሲሆን ዩኤንዲፒ በኢትዮጵያ በአይቲ ዘርፍ ለጀማሪና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በሚያደርገው ድጋፍ ለሚቀርበው ብድር በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል ዋስትናን ለመስጠት የሚያስችል ነው ተብሏል።
ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በስምምነቱ መሰረት አንድ ሚሊዮን ዶላር የብድር ዋስትና ፈንድ የተዘጋጀ ሲሆን የኢትዮጵያ ልማት ባንክም የብድር ዋስትናውን የሚያስተዳድር ይሆናል።
የብድር ዋስትና ፈንድ ማስተዳደር ስምምነቱን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሃንስ አያሌው እና የመንግስታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ቱርሃን ሳሌህ ናቸው የተፈራረሙት።
በአይቲ ዘርፍ ለጀማሪና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ድጋፍ የሚያደርገውን ፕሮጀክት የመንግስታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በጋራ እንደሚተገብሩትም ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሃንስ አያሌው ባንኩ ለአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን በመጥቀስ ያሁኑ ፕሮጀክትም በዚሁ ዘርፍ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው ብለዋል።
ከፈጠራ ስራዎች ጋር ተያይዞ የአይዲያ ፋይናንሲንግ ስራን በሰፊዉ ለመተግበር በዳይሬክቶሬት ደረጃ ክፍል መደራጀቱን የገለጹት ዶክተር ዮሃንስ ባንኩ ጀማሪዎችን በፋይናንስ በመደገፍ ውጤታማ የሚሆኑበትን የአሰራር ሂደት ማዘጋጀቱን አብራርተዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም የኢትዯጵያ ዳይሬክተር ቱርሃን ሳሌህ በበኩላቸው ለጀማሪዎችም ሆነ ለአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ አቅርቦት ወሳኙ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከዩኤንዲፒ ጋር በታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂ ማስፋፋትና ማስተዋወቅ ፕሮጀክት ላይ ተሰርቶ ከፍተኛ ውጤት ማሳየቱንና ይህም ስምምነት በኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዙሪያ ለሚንቀሳቅሱ ጀማሪና ነባር የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በተመሳሳይ መንገድ ለመተግበር የተሰናዳ ነው ብለዋል።
በስምምነቱ ላይ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ባይሳ በዳዳ እንዲሁም የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ባስተላለፉት መልእክት ለፕሮጀክቱ መሳካት አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል የሚያደርጉ መሆኑን አረጋግጠዋል።