ቀጥታ፡

የዓለም ዋንጫ አሸናፊው የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን ቦነስ አይረስ ከተማ ሲደርስ ደማቅ አቀባበል ተደረገለት

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 11/2015 የ22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ አሸናፊ የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን ትናንት እኩለ ሌሊት ላይ ቦነስ አይረስ ከተማ ሲደርስ በሺዎች የሚቆጠሩ አርጀንቲናውያን ደማቅ አቀባበል አድርገውለታል።

ከትናንት በስቲያ በዓለም ዋንጫ ፍጻሜ የአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድንን በመለያ ምት 4 ለ 2 በማሸነፍ ለሶስተኛ ጊዜ ዋንጫውን አንስታለች።

በአርጀንቲናዊው ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ የሚመራውን ብሔራዊ ቡድን የያዘው አውሮፕላን ትናትን ከሌሊቱ 8 ሰአት ከ40 ቦነስ አይረስ ከተማ በሚገኘው ኢዜይዛ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ መድረሱን አልጄዚራ ዘግቧል።

የአርጀንቲና ተጫዋቾች እኩለ ሌሊቱን በአየር ማረፊያ አቅራቢያ በሚገኘው የአገሪቷ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ውስጥ በሚገኘው የልምምድ ስፍራ ማሳለፋቸው ተገልጿል።

ዛሬ በአርጀንቲና የሰአት አቆጣጠር ከቀኑ ስድስት ሰአት (በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከምሽቱ 12 ሰአት ጀምሮ) ከቦነስ አይረስ ማዕከላዊ ቦታ (ሲቲ ሴንተር) በመነሳት በሚሊዮን በሚቆጠሩ አርጀንቲናውያን ታጅበው ከተማውን እንደሚዞሩ ተነግሯል።

የ63 ዓመቱ የአርጀንቲና ፕሬዝዳንት አልቤርቶ አንጌል ፈርናንዴዝ የዛሬውን ቀን ብሔራዊ ክብረ-በዓል እንዲሆን ማወጃቸውን አልጄዚራ በዘገባው አመልክቷል።

በተያያዘ ዜና በዓለም ዋንጫ ፍጻሜው በአርጀንቲና የተሸነፈው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ትናንት ማምሻውን ፓሪስ ሲደርስ ደማቅ አቀባበል እንደተደረገለት ቢቢቢ በድረ ገጹ ባወጣው መረጃ አስፍሯል።

በፍጻሜው ጨዋታ ሦስት ጎሎችን በማስቆጠር ሀትሪክ የሠራው ኪሊያን ምባፔ ከፊት ሆኖ ታይቷል።

ደጋፊዎች በፓላስ ዴ ላ ኮንኮርድ ርችቶችን መተኮሳቸውን ቢቢሲ በዘገባው አስነብቧልል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም