የአልባሳትና ጨርቃጨርቅ ምርት በኢኮኖሚው ውስጥ የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የአልባሳትና ጨርቃጨርቅ ምርት በኢኮኖሚው ውስጥ የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎች ገለጹ
ሐዋሳ (ኢዜአ) ታህሳስ 11/2015 የአልባሳትና ጨርቃጨርቅ ዘርፍ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የላቀ አስተዋጽኦ የማበርከት ተስፋ እንዳለው በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎች ገለጹ።
በኢትዮጵያ የተደረሰው የሰላም ስምምነት ሥራቸውን በተስፋና በልበ ሙሉነት እንዲቀጥሉ ያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ የነበራቸው በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በሥራ ላይ የሚገኙ ኩባንያዎች የሥራ ኃላፊዎች እንደገለፁት፤ በመንግስትና በህወሃት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ሥራቸውን በልበ ሙሉነት እንዲቀጥሉ የሚያደርግ ተስፋ ይዞ የመጣ ነው፡፡
እ.አ.አ ከ2017 ጀምሮ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ የጀመረው የሲልቨር ስፓርክ አልባሳት ኩባንያ በኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጎፓል ክሪሽና ኩባንያቸው በአሁኑ ወቅት ከ2 ሺህ 700 በላይ ሠራተኞችን ይዞ በቀን ሶስት ሺህ የወንዶች ሙሉ ልብስ በማምረት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ምርታቸውን ወደ አሜሪካ ገበያ እየላኩ እንደሆነ ገልጸው፤ የኩባንያውን የማምረት አቅም የማሳደግና በስፋት ወደ ገበያ የመግባት ፍላጎት እንዳላቸውም ተናግረዋል።
የሠላም ሥምምነቱ ለባለሀብቶች ብዙ ተስፋ ይዞ የመጣ፤ ሥራቸውንም በልበ ሙሉነት እንዲቀጥሉ ያደረገ እንደሆነ በመጥቀስ፤ በአሁን ወቅት በፓርኩ ውስጥ ተጨማሪ የማስፋፊያ ሥራዎችን ለመስራት ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ባለሀብቶቹን ለማበረታታት የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውንና በአፍሪካና አውሮፓ ሀገራት ገበያ ለማፈላለግ እየተደረገ ያለው ጥረትም ተጨማሪ ተስፋ እንደሆናቸው አስረድተዋል ፡፡
ኢትዮጵያ በአልባሳትና ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ትልቅ ተስፋ እንዳላትም አንስተው በማጠናከር ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦውን ለማሳደግ በትኩረት መሰራት እንዳለበት አመልክተዋል።
ከ5 ሺህ 200 በላይ ሰራተኞችን በመያዝ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በአልባሳትና ጨርቃጨርቅ ዘርፍ ላይ የተሰማራው የኢንዶቺን አልባሳት ኩባንያ የኦፕሬሽናል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሄማንታ ሀሪሽቻንድራ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የውስጥ ሠላም መጠናከር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።
የሰላም ስምምነቱ በዓለም ዙሪያ ካሉ ደንበኞቻቸው ጋር ዘላቂ የሆነ ትሥሥር ለመፍጠርና ተጨማሪ አዳዲስ ሥራዎችን ለመስራት ዕድል የሚከፍት እንደሆነ ነው የተናገሩት ፡፡
በአሁን ወቅት ኩባኒያቸው በወር 1 ሚሊዮን 500 ሺህ አልባሳትን የማምረት አቅም እንዳለው ገልፀው ተጨማሪ ትዕዛዞችን ስናገኝ ሥራችንን የማስፋፋትና ተጨማሪ ሠራተኞችን የመቅጠር ዕድላችን ይሰፋል ብለዋል ፡፡
በኢትዮጵያ የሥራ አቅም ያለው የሰው ኃይል እንዳለ የተናገሩት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ ለአልባሳትና ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ማደግ መልካም ዕድሎች እንንዳሉ ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ያለውን የኢንዱስትሪውን አቅም አስተባብሮ በመጠቀም አገሪቱ ከውጭ የምታገኘውን ገቢ ማሳደግ እንደሚገባም አመልክተዋል ፡፡
የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ማቴዎስ አሸናፊ በፓርኩ የተሰማሩ ኩባንያዎችን የገበያ አማራጭ ለማስፋት በተደረገው የተቀናጀ ጥረት ገበያቸውን ወደ አውሮፓ፣ እሲያና አፍሪካ ሀገራት እንዲያሰፉ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
የሠላም ስምምነት መደረጉ ለባለሀብቶቹ ትልቅ ተስፋ መሆኑን ጠቅሰው፤በአሁን ወቅት በተለይ የተለያዩ ሀገራት ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እያሳደሩ እንደሆነ ገልጸዋል።
በፓርኩ ውስጥ በሥራ ላይ ያሉ ኩባንያዎችም አቅማቸውን ለማስፋፋት ተጨማሪ ሼዶችና የሰራተኛ ቅጥር እንዲፈፀምላቸው ጥያቄ እያቀረቡ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በአሁን ወቅት 24 ኩባኒያዎች ያሉ ሲሆን ከ28 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸው በሥራ ላይ እንደሚገኙ ከፓርኩ የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡