የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ከኢትዮጵያ ቡና የሚያደርጉት የዛሬ ጨዋታ ተጠባቂ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ከኢትዮጵያ ቡና የሚያደርጉት የዛሬ ጨዋታ ተጠባቂ ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 11/2015 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ከኢትዮጵያ ቡና ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከምሽቱ 1 ሰአት በድሬዳዋ ስታዲየም ይደረጋል።
ከስምንት ዓመት በኋላ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የተመለሰው ኢትዮጵያ መድን በውድድር ዓመቱ ጥሩ ግስጋሴ በማድረግ ላይ ይገኛል።
በዚህም በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው 12 ጨዋታዎች ሰባት ጊዜ ሲያሸንፍ በሶስት ጨዋታዎች ተሸንፎ በሁለት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይቷል።
በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራው ኢትዮጵያ መድን 23 ነጥብ በመሰብሰብ ፕሪሚየር ሊጉን እየመራ ይገኛል።
የኢትዮጵያ መድን ተጋጣሚ የሆነው ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ በዘንድሮው የውድድር ዓመት እያሳየ ያለው ብቃት ለክለቡ ደጋፊዎች አስደሳች የሚባል አይደለም።
ኢትዮጵያ ቡና እስከ አሁን በሊጉ ባደረጋቸው 10 ጨዋታዎች አራት ጊዜ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ አራት ጊዜ ተሸንፎ ሁለት ጊዜ ደግሞ በአቻ ውጤት ተለያይቷል።
በሊጉ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች እየቀረው በ14 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይም ይገኛል።
ከሁለቱ ክለቦች የዛሬ ጨዋታ ቀደም ብሎ ከቀኑ 10 ሰአት ፋሲል ከነማ ከወልቂጤ ከተማ በድሬዳዋ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በፕሪሚየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ወልቂጤ ከተማ በ16 ነጥብ ሰባተኛ፤ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ፋሲል ከነማ በ15 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ትናንት በተደረጉ 13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መቻል ባህርዳር ከተማን 3 ለ 2 ሲረታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከሀዲያ ሆሳዕና ያደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።