ቀጥታ፡

የድሬዳዋ ደረቅ ወደብ ቀጣና በቀን ከ150 በላይ የጭነት ተሽከርካሪዎችን እያስተናገደ ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 11 /2015 የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ለማሳለጥ የተገነባው ዘመናዊ ደረቅ ወደብ በቀን ከ150 በላይ የጭነት ተሽከርካሪዎችን እያስተናገደ መሆኑን የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ገለጸ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለኢትዮጵያና ለቀጣናው አገራት የገቢና ወጭ ንግድ መሳለጥ የጎላ አበርክቶ ይኖረዋል የተባለውን የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና በይፋ ማስጀመራቸው ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሮባ መገርሳ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ነፃ የንግድ ቀጣና ደንበኞቹን በቅርበት ማግኘት የሚችልበት መሰረተ-ልማት ነው፡፡

በቀጣናው ከሚሰጡ አገልግሎቶች መካከል አንዱ ሎጀስቲክስ በመሆኑ ዓላማውን ሊያሳካ የሚችል ዘመናዊ ደረቅ ወደብ መገንባቱን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በቀጣናው ውስጥ ነፃ የንግድ አገልግሎት የሚሰጥ የሎጀስቲክስ መሰረተ-ልማት ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና በቅርበት አገልግሎት ለማግኘት ከማስቻሉም ባለፈ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘትና የስራ ዕድል በመፍጠር የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የንግዱ ማህበረሰብ አባላትም ወደ ገበያው በመግባት በትብብርና በቅንጅት ሊሰሩበት የሚገባ ፕሮጀክት መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውና በጥራቱም በአፍሪካ ምርጥ የሚባለው የድሬዳዋ ደረቅ ወደብ ቀጣና የተቋቋመለትን ዓላማ ለማሳካት የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የሎጀስቲክስ ዘርፉን በማዘመን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችለውን እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑንም ጨምረው አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም