ቀጥታ፡

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ኤጀንሲ የግብርና ግብዓቶች ግዥ ክፍያን በዲጂታል ለመፈጸም የሚያስችለውን ሥምምነት ከንግድ ባንክ ጋር ተፈራረመ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 10/2015 የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ኤጀንሲ የግብርና ግብዓቶች ግዥ ክፍያን በዲጂታል ለመፈጸም የሚያስችለውን ሥምምነት ከንግድ ባንክ ጋር ተፈራረመ።

ሥምምነቱን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖና የኤጀንሲው ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት አሰፋ ፈርመውታል።    

ሥምምነቱ አርሶ አደሮች ለግብርና ግብዓት የሚያስፈልገውን ማዳበሪያ፣ ኬሚካልና ምርጥ ዘር በንግድ ባንክ በኩል ግዥዎችን ዲጂታል ለመፈጸም የሚያስችል ነው ተብሏል።   

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ እንደገለጹት፤ ሥምምነቱ አርሶ አደሩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ ነው።

አሰራሩ አርሶ አደሩ ባንክ መሄድ ሳይጠበቅበት ዲጂታል በሆነ መንገድ በሞባይል ስልክ ክፍያ መፈጸም የሚያስችለውን መሆኑን ጠቁመዋል።  

ይህም ጊዜ ቆጣቢና አዋጭ የቴክኖሎጂ ሥርዓት መሆኑን አስረድተዋል።  

ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት፤ ባንኩ በዚህ ሥምምነት መሰረት አርሶ አደሮችን ለማስተናገድ ቅርንጫፎችን ከመጠቀም ባለፈ በወኪሎች በኩል አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት አድርጓል።    

አሰራሩ በሁለት አይነት መንገድ እንደሚተገበር የገለጹት አቶ አቤ ከአሰራሩ አንዱ አርሶ አደሮች በባንኩ ካስቀመጡት ገንዘብ ላይ በሞባይል ክፍያ መፈጸም የሚችሉበት ነው።   

ሁለተኛው ደግሞ "ዋሌት" የተሰኘ የሞባይል አገልግሎት ሲሆን አርሶ አደሮች የባንክ ሂሳብ መክፈት ሳይጠበቅባቸው በወኪሎች በኩል በሚከፈትላቸው የሲ ቢ ኢ አገልግሎት ነው።  

ዋሌት በተሰኘው አገልግሎት አርሶ አደሮች እስከ 30 ሺህ ብር ድረስ ማስቀመጥ የሚችሉ ሲሆን አርሶ አደሩ የሚፈልገውን ግብዓት በዚህ አሰራር በኩል ማግኘት እንደሚችል ጠቁመዋል።  

ፕሬዝዳንቱ እንደሚሉት፤ አርሶ አደሩ በዘር ወቅት የግብርና ግበዓት ግዥ ለመፈጸም የሚያባክነውን ጊዜ ማስቀረት የሚቻል ሲሆን የቁጠባ ባህሉንም የሚያሳድግ ነው ብለዋል።   

አሰራሩ ከዚህ ባለፈም የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ኤጀንሲ ከአርሶ አደሩ በአግባቡ ክፍያውን መሰብሰብ እንደሚያስችለውም ነው የገለጹት።    

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ኤጀንሲ ሃላፊ ወይዘሮ መሰረት አሰፋ በበኩላቸው በቀበሌ ደረጃ ያሉ መሰረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ከአርሶ አደሩ በጥሬ ገንዘብ እንደሚሰበስቡ አስታውሰዋል።     

በጥሬ ገንዘብ መሰብሰቡ አዋጭ አይደለም ያሉት ሃላፊዋ ሥምምነቱ አርሶ አደሩ በሞባይል ክፍያ እንዲፈጽም የሚያደርግ በመሆኑ ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።      

ሥምምነቱ በቀጣይም የግብርና ግብዓትን በተመለከተ የሚፈጸሙ ክፍያዎች በቴክኖሎጂ ብቻ የተደገፈ እንዲሆን ለሚደረገው ጥረት መሰረት የሚጥል እንደሆነም ተናግረዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም