ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ በማኅበር ቤት ለሚገነቡ ቆጣቢዎች ብድር ማቅረብ የሚያስችለውን ሥምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 10/2015 የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ በማኅበር ተደራጅተው ቤት ለሚገነቡ ብድር ማቅረብ የሚያስችለውን ሥምምነት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ተፈራረመ።

ሥምምነቱን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ያስሚን ወሃብረቢና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ ዛሬ ፈርመውታል።  

የቢሮ ሃላፊዋ ወይዘሮ ያስሚን እንዳሉት፤ ሥምምነቱ ከዚህ በፊት የተመዘገቡና በማህበር የተደራጁ ቆጣቢዎች 70 በመቶ ቆጥበው 30 በመቶ ከንግድ ባንክ በሚያገኙት ብድር ቤት መገንባት እንዲችሉ የሚያስችል ነው።    

ከተማ አስተዳደሩ ፍላጎት ያላቸውን 12 ሺህ ቆጣቢዎች ከዚህ በፊት በኦንላይን ምዝገባ ማካሄዱን ጠቁመው መረጃቸውን አሟልተው ዝግጁ የሆኑ ከ4 ሺህ 500 በላይ ቆጣቢዎች መገኘቱን ገልጸዋል።

እነዚህ ቆጣቢዎቹ ግንባታውን የሚያካሂዱበት ከ30 ሄክታር በላይ መሬት ዝግጁ መደረጉን የተናገሩት ሃላፊዋ የግንባታ ዲዛይን ዝግጅት መጠናቀቁንም አብራርተዋል።

እንደ ወይዘሮ ያስሚን ገለጻ 70/30 የቤቶች መርሃ ግብር በተለይም እየጨመረ የመጣውን የቤት ፍላጎት ለማሟላት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው።   

ከተማ አስተዳደሩ ባለፉት 18 ዓመታት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር አብሮ በመሥራት ውጤታማ ሥራዎችን ማከናወኑን አስታውሰው ዛሬ ያደረግነው ሥምምነትም በቀጣይ በፋይናንስ በኩል የሚገጥሙ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል።  

ቢሮው ቆጣቢ ማኅበራት የሚገነቡት ቤት በሚፈለገው ጊዜ እንዲጠናቀቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።       

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በማኅበር የተደራጁ ቆጣቢዎች በሚቻለው ፍጥነት ቤት ገንበተው ባለቤት እንዲሆኑ ባንኩ አስፈላጊውን ርብርብ ያደርጋል።

በርካታ ቤት ፈላጊዎች በቢሊዮን የሚቆጠር ብሮች የቆጠቡ ደንበኞች መኖራቸውን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ እንደዚህ ዓይነት መርሃ ግብር መጀመሩ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደተናገሩት ከተማ አስተዳደሩ ከንግድ ባንክ ጋር በመሆን በ10 ዘጠና፣በ20 80 እና 40 60 መርሃ ግብሮች ከ300 ሺህ በላይ ቤቶች ተገንብተው ለተጠቃሚዎች ተላልፈዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም