ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በአትሌቲክስ ዘርፍ ብቃት ያላቸው ወጣቶችን ለማፍራት እየሰራ ነው

አዲስ አበባ /ኢዜአ/ ታህሳስ  10/2015 የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በአጭር እርቀትና በሜዳ አትሌቲክስ ተግባራት ብቃት ያላቸው ወጣቶችን ለማፍራት እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ከተቋቋመለት ዓላማ አንዱ ወጣት ስፖርተኞችን በማብቃት ለክለቦችና ለብሔራዊ ቡድን መጋቢ መሆን ነው።

አካዳሚው አሁን ላይ በ10 የስፖርት ዓይነቶች የስፖርት ሥልጠና በመሥጠት በርካታ ስፖርተኞችን በማፍራትም ላይ ይገኛል።

የአካዳሚው የትምህርት፣ የውድድርና ሥልጠና ዳይሬክተር አብዮት ተስፋዬ፤ በአትሌቲክስ ዘርፍ በአጭር ርቀት፣ በሜዳ ላይ ተግባርና ሌሎችም የስፖርት አይነቶች ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

በአጭር እርቀትና በሜዳ ላይ የአትሌቲክስ ተግባራት በተለያዩ ውድድሮች ሠልጣኞች እያስመዘገቡት ያለው ውጤት ለዘርፉ እድገት ትልቅ ተስፋ የሰነቀ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከአጭር እርቀት በተጨማሪ በሜዳ ላይ የአትሌቲክስ ተግባራት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው በውርወራ ስፖርትም አዲስ አበባ በሚገኘው የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ስልጠና መስጠት መጀመሩን ገልጸዋል ።

በቀጣይም በረጅም እርቀት ያላትን ታሪክ በአጭር እርቀትና በሜዳ ላይ ተግባርም የአትሌቲክስ ውጤታማነትን ለማሳዳግ ክለቦች ከአካዳሚው የሚወጡ ሰልጣኞች በመቀበል በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው ነው የተናገሩት።

ከአካዳሚው የሚወጡ ሠልጣኞች በቂ ሥልጣናና ትኩረት ተሰጥቶት ከተሰራ በአጭር እርቀትና የሜዳ ላይ ተግባር በአህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮች አቅም ያላቸው በርካታ አትሌቶችን ማፍራት እንደሚቻል ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም