ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የጀመረቻቸውን ጥረቶች የሚያጠናክር ንቅናቄ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታኅሳስ 10/2015 ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የጀመረቻቸውን ጥረቶች ማጠናከርን ያለመ ሀገር አቀፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐግብር ከመጪው ረቡዕ ጀምሮ እንደሚካሄድ ተገለጸ።

ዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት በሰጠው መግለጫ መርሃ ግብሩ "የተሻሻሉ ማጣጣሚያ ስልቶች ለአየር ንብረት ለውጥ ስርዓት ግንባታ በኢትዮጵያ" በሚል መሪ ቃል ለሦስት ወራት በመላ ሀገሪቱ ይካሄዳል።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ በዜጎች ላይ የሚያደርሰውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ለመግታት የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ናት።

ለዚህም ባለፉት አራት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ህዝብን በንቃት በማሳተፍ ከ20 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል እንዲሁም በታዳሽ ኃይል ልማት ላይ በማተኮርም ከባቢ አየር እንዳይበከል የበኩሏን እየተወጣች ትገኛለች።

ሀገር አቀፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐግብሩ የሚካሄደው የኢትዮጵያን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን የመቋቋም ተግባራትን ለማጠናከርም መሆኑ ተገልጿል።

የዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት ፕሮጀክት አስተባባሪ ወይዘሮ መድህን ፍስሐ፤ በመርሃ ግብሩ ላይ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ በኢትዮጵያና የመቋቋሚያ ተግባራት ላይ  ያተኮረ ሀገር አቀፍ ጥናት ይፋ እንደሚሆን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ልማት ስራዎች የሚያስቃኝ አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ የሚካሄድ መሆኑን ገልጸው ከ30 ሺህ በላይ ሰዎች እንደሚመለከቱትም ይጠበቃል ብለዋል።

መርሐግብሩ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚካሄድ ሲሆን ውይይቶችና ኤግዚቢሽኖችም እንደሚካሄዱ ጠቁመዋል ።

ዜጎች በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያላቸው አረዳድ እንዲያድግ ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም ገልጸዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን እንዲሁም ዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት መርሐግብሩን በጥምረት አዘጋጅተውታል።

የፌደራልና የክልል የዘርፉ አመራሮች፣  የፈጠራ ባለሙያዎች፣ በመስኩ የተሰማሩ ተመራማሪዎች እንዲሁም በታዳሽ ኃይል የሚሰሩ ተቋማት እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም