ቀጥታ፡

ባለፉት አምስት ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ የሥጋ ምርት ከ41 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 10/2015 ባለፉት አምስት ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ የሥጋ ምርት ከ41 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ገለጸ።

በበጀት ዓመቱ 28 ሺህ ቶን የሥጋ ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑንም ባለሥልጣኑ ጠቁሟል።  

በባለሥልጣኑ የኤክስፖርት ቄራ ኢንስፔክሽንና ሰርተፊኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር አያሌው ሹመት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ባለፋት አምስት ወራት ወደ ውጭ ከተላከ የሥጋ ምርት 41 ሚሊየን 800 ሺህ ዶላር ገቢ ተገኝቷል።

ገቢው የተገኘው 5 ሺህ 900 ቶን የሥጋ  ምርት በማቅረብ  መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የሥጋ ምርቱ በስፋት ከተላከባቸው አገራት መካከል ዱባይ፣ ሳዑዲ አረቢያና ኩዌት እንደሚገኙበት ነው የገለጹት።

በተጓዳኝም በተያዘው በጀት ዓመት 28 ሺህ ቶን የሥጋ ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑንም ነው የጠቀሱት።

በዚህም ከ150 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ይገኛል ተብሎ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሥጋ ምርቱ ጥራቱን ጠብቆ በብዛት ለገበያ እንዲቀርብ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም  ተናግረዋል።

በተለይም በቻይና፣ ኢንዶኔዥያ፣ እንዲሁም በአውሮፓ አገራት ለመግባት የሚያስችሉ ጥረቶች እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል።

አሁን ባለ አቅም በየዓመቱ 200 ሺህ ቶን የሥጋ ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደሚቻል ጠቁመው፤ ይህንንም እውን ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በአገር ውስጥ ያለውን ከፍተኛ የሥጋ ፍላጎት ለማሟላት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ አንጻር አሁን የተጀመረው የሌማት ትሩፋት ይህን ክፍተት በመሙላት ረገድ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ እንደሚሆንም አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 70 ነጥብ 2 ሚሊየን የቀንድ ከብት 42 ነጥብ 9 ሚሊየን የበግ፣ 8 ሚሊየን የግመል እንዲሁም 52 ሚሊየን አካባቢ የፍየል ሃብት መኖራቸውን ከባለሥልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም