ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት መርሐግብር ዛሬ በሚካሄዱ ጨዋታዎች ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት መርሐግብር ዛሬ በሚካሄዱ ጨዋታዎች ይጀመራል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 10/2015 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት መርሐግብር ዛሬ በሚካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል።
በዓለም ዋንጫው ምክንያት ተቋርጦ የነበረው ፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች የዲኤስቲቪ የቀጥታ ስርጭት እንደሚጀመርም ተገልጿል።
ባህር ዳር ከተማ ከመቻል ከቀኑ 10 ሰአት እንዲሁም ኢትዮ ኤሌትሪክ ከሀድያ ሆሳዕና ከምሽቱ 1 ሰአት በድሬዳዋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ነገ ፋሲል ከነማ ከወልቂጤ ከተማ ከቀኑ 10 ሰአት፤ከምሽቱ 1 ሰአት ኢትዮጵያ ቡና ከፕሪሚየር ሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ጋር ይጫወታሉ።
የፕሪሚየር ሊጉ 13ኛ ሳምንት መርሐግብር እስከ ታህሳስ 13 ቀን 2015 ዓ.ም ይቆያል።
በኳታር አስተናጋጅነት ሲካሄድ በቆየው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ምክንያት ዲኤስቲቪ አቋርጦት የነበረውን የሊጉ ጨዋታዎች የቀጥታ ስርጭት ዛሬ እንደሚጀመር የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል።
የ13ኛ ሳምንት ሁሉም ጨዋታዎች የቀጥታ ስርጭት ሽፋን እንደሚያገኙም ገልጿል።
የፕሪሚየር ሊጉን የደረጀ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ መድን በ23 ነጥብ እየመራ ነው።
ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህር ዳር ከተማ በተመሳሳይ 22 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ሲዳማ ቡና፣ኢትዮ ኤሌትሪክ እና ለገጣፎ ለገዳዲ ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለወን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።
የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን ቡርኪናፋሶዋዊው የቅዱስ ጊዮርጊስ የፊት መስመር ተጫዋች ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ በ11 ግቦች ይመራል።
የወልቂጤ ከተማው ጌታነህ ከበደ በ10 ግቦች ይከተላል።
የፋሲል ከነማው ፍቃዱ ዓለሙ እንዲሁም የድሬዳዋ ከተማው ቢኒያም ጌታቸው በተመሳሳይ ሰባት ግብ አላቸው።