ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ በአፋር ክልል በኩዌት ባለሀብቶች እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን ጎበኙ

ታህሳስ 10/2015 (ኢዜአ) የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አዋል አርባ በክልሉ በኩዌት ባለሀብቶች በ 5 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እየተካሄደ ያለውን የእርሻ ልማት ስራዎች ጎበኙ።

የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ በአይሳኢታ ወረዳ በኩዌት ባለሀብቶች በ አምስት ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እየተካሄደ ያለውን የእርሻ ልማት ስራዎች ጎበኝተዋል።

የኩዌት ባለሀብቶች በአይሳኢታ ወረዳ በዘመናዊ ቴክኖሊጂ በመታገዝ በ 5 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ፣ በቆሎ፣ የእንስሳት መኖ እና ሌሎች ምርቶችን ለማምረት በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።

የእርሻ ልማቱን የጎበኙት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ በመከናወን ላይ ያለውን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የእርሻ ልማት ስራ አድንቀው ወደ ሌሎች ወረዳዎችም ተሞክሮውን በማስፋት የምግብ ዋስትናችንን ለማረጋገጥ ፊታችንን ወደ እርሻ ልማት ልናዞር ይገባል ብለዋል።

የኩዌት ባለሀብቶች በበኩላቸው የእርሻ ልማቱን በድርጅታቸው ብቻ የሚወሰን ሳይሆን የአካባቢው ማህበረሰብንም ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት የእርሻ ልማት ስራ እንዲያከናውኑ ለማድረግ እቅድ እንዳላቸው ገልፀዋል።

በምግብ ራስን ለመቻል እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ይበልጥ ለማጠናከር እና ውጤታማ ለማድረግ የክልሉ መንግስት ድጋፍና ክትትል በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ከአፋር ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም