ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን አሰላ ቅርንጫፍ ጥራታቸውን የጠበቁ 11 አይነት ምርጥ የሰብል ዝርያዎችን እያቀረበ ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 9/2015 በኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን አሰላ ቅርንጫፍ ጥራታቸውን የጠበቁና በሽታ የሚቋቋሙ 11 አይነት ምርጥ የሰብል ዝርያዎችን በማባዛት ለአርሶ አደሮች እያቀረበ መሆኑን ገለጸ።

የኮርፖሬሽኑ የአሰላ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ብርሃኑ የሺጥላ፤ በራሱ እርሻ ቦታና በክላስተር ከተደራጁ አርሶ አደሮችና ባለሃብቶች ጋር በመተባበር ተቋሙ የዘር ማባዛት ስራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የዘር ማባዛቱ በዋናነት በጤፍና ስንዴ ላይ የሚደረግ ሲሆን አተር፣ ምስር፣ ባቄላና ከቅባት እህሎችም መካከል የጎመን ዘርና ተልባ የዘር ብዜት እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው የዘር ብዜት ከሚከናወንባቸው 11 የሰብል አይነቶች ከ30 በላይ ዝርያዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።

የአሰላ ቅርንጫፍ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን በ2014/15 ዓ.ም 1 ሺህ 511  ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን አቅዶ 2 ሺህ 995 ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን ከእቅዱ በላይ አሳክቷል።

በአሰላ ቅርንጫፍ በዘር ከተሸፈነው 10 ሺህ 214 ኩንታል ምርጥ ዘር የተገኘ ሲሆን በቀጣይ ተጨማሪ 42 ሺህ 500 ኩንታል ምርጥ ዘር ይጠበቃል ብለዋል።

በተለይ የጤፍ ምርጥ ዘር በማባዛት ለህብረሰቡ ተደራሽ በማድረግ ላይ ሲሆን በዓመት እስከ 30 ሺህ ኩንታል የጤፍ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች እያከፋፈለ መሆኑን ነው የገለጹት። 

በኮርፖሬሸኑ የዘር ዝግጅት መምሪያ ስራ አስኪያጅ አቶ ዘነበ ጌታቸው፤ አርሶ አደሮች ምርጥ ዘር በመጠቀማቸው ብቻ እስከ 30 በመቶ ምርታማነታቸውን እንደሚጨምር አስረድተዋል።

ኮርፖሬሽኑ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከሚገኙ የምርጥ ዘር ማባዣ ማዕከላት በዘር ከተሸፈነው 120 ሺህ ኩንታል ሰብል መሰብሰቡን ገልጸዋል።

የተሰበሰበው ምርጥ ዘር 30 በመቶ ብቻ መሆኑን ጠቅሰው ቀሪው 70 በመቶ ምርጥ ዘር በመሰብሰብ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ አርሶ አደሮችና ሰፋፊ እርሻ ያላቸው ባለሀብቶች ምርጥ ዘር የመጠቀም ፍላጎታቸው እየጨመረ ሲሆን ከሀገሪቱ የምርጥ ዘር አቅርቦት ኮርፖሬሽኑ 30 በመቶውን እየሸፈነ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ምርጥ ዘር ከማቅረብ በተጨማሪ ለአርሶ አደሮች፣ ባለሃብቶች እና የልማት ድርጅቶች የግብርና ማሳደጊያ ግብዓቶችና ሌሎች የግብርና ሜካናይዜሽን የሚውሉ ማሽነሪዎችን ያቀርባል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም