ቀጥታ፡

ኮከቡ ሊዮኔል ሜሲ ወይስ ኪሊያን ምባፔ ትልቁን የእግር ኳስ ክብር የሚያሰጠውን ዋንጫ ማን ያነሳል ?

አዲስ አበባ ታህሳስ 9/2015 (ኢዜአ) 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ የእግር ኳሱ ኃያላኑ አርጀንቲና እና ፈረንሳይ ትልቁን የእግር ኳስ ክብር የሚያሰጠውን ዋንጫ ለማንሳት ይፋለማሉ።

አርጀንቲና ከ36 ዓመት በኋላ የዓለም ዋንጫውን ታሸንፋለች? ወይስ ፈረንሳይ ለተከታታይ ጊዜ ዋንጫውን ከፍ ታደርጋለች?።

የዓለም ህዝቦች ለ90 ደቂቃ፣120 ደቂቃ ምናልባትም ከዛ በላይ ቀልባቸውን ልባቸውን ወደ ሉሳይል ስታዲየም ያደርጋሉ።

የእግር ኳሱ ኃያላን አርጀንቲና እና ፈረንሳይ በዓለም ዋንጫ ሲገናኙ የአሁኑ ለአራተኛ ጊዜ ነው።

ኡራጓይ እ.አ.አ በ1930 ባዘጋጀችው የመጀመሪያው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በምድብ አንድ ተገናኝተው አርጀንቲና ሉዊስ ፍሊፔ ሞንቲ በ81ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ ፈረንሳይን 1 ለ 0 አሸንፋለች።

ከ48 ዓመት በኋላ እ.አ.አ በ1978 አርጀንቲና ባዘጋጀችው 11ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ዳንኤል ፓሳሬላ በፍጹም ቅጣት ምት እንዲሁም ሊኦፖልዶ ሉኬ በጨዋታ ባስቆጠሯቸው ግቦች አርጀንቲና ፈረንሳይን 2 ለ 1 ማሸነፏ የሚታወስ ነው።

ሚሼል ፕላቲኒ በወቅቱ ለፈረንሳይ ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረ ተጫዋች ነበር።

አርጀንቲና ኔዘርላንድስን በማሸነፍ የ11ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ መሆን ቻለች።

ሁለቱ አገራት ለመጨረሻ ጊዜ በዓለም ዋንጫው የተገናኙት ከአራት ዓመት በፊት ሩሲያ ባዘጋጀችው 21ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ነበር።

በጥሎ ማለፉ(16ት ውስጥ) ተገናኝተው ፈረንሳይ አርጀንቲናን 4 ለ 3 በማሸነፍ ለሩብ ፍጻሜ አልፋለች።

ኪሊያን ምባፔ ሁለት ግቦች ሲያስቆጥር አንቶኒዮ ግሪዝማን በፍጹም ቅጣት ምት እንዲሁም ቤንጃሚን ፓቫርድ በጨዋታ ቀሪዎቹን ግቦች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

አንጌል ዲማሪያ፣ጋብርኤል ሜርካዶ እና ሰርጂዮ አጉዌሮ በወቅቱ ለአርጀንቲና ግቦቹን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።

በአጠቃላይ ሁለቱ አገራት እስከ አሁን 12 ጊዜ ተገናኝተው አርጀንቲና ስድስት ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዛለች።

ፈረንሳይ ሶስት ጊዜ አሸንፋለች። ሶስት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።በ12ቱ ጨዋታዎች 26 ግቦች ከመረብ ላይ አርፈዋል።

አርጀንቲና 15 እንዲሁም ፈረንሳይ 11 ግቦችን አስቆጥረዋል።አርጀንቲና እና ፈረንሳይ በዓለም ዋንጫ ስኬታማ የሚባል የውድድር ታሪክ አላቸው።አርጀንቲና የዘንድሮውን ጨምሮ በዓለም ዋንጫው ለ18 ጊዜ ተሳትፋለች።

የዛሬውን ጨምሮ በውድድሩ ለፍጻሜ ስትደርስ ለስድስተኛ ጊዜ ነው።እ.አ.አ በ1930፣1978፣1986፣1990 እና 2014 ለፍጻሜ የደረሱባቸው ዓለም ዋንጫዎች ናቸው።አርጀንቲና እ.አ.አ 1978 እና 1986 የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ሆናለች።

ፈረንሳይ የዘንድሮውን ጨምሮ በዓለም ዋንጫው 16 ጊዜ ተሳትፋለች። የዛሬውን ጨምሮ ለአራት ጊዜ ለፍጻሜ ደርሳለች።ከአራት ዓመት በፊት በሩሲያ በተዘጋጀው 21ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ፈረንሳይ ክሮሺያን 4 ለ 2 አሸንፋ ዋንጫውን ለሁለተኛ ጊዜ አንስታለች።

ሰማያዊዎቹ እ.አ.አ በ1998 ባዘጋጁት 16ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ብራዚልን 3 ለ 0 በማሸነፍ የመጀመሪያውን ዋንጫ ማንሳቷ የሚታወስ ነው።

በዛሬው ጨዋታ የእግር ኳስ ቤተሰቡን ቀልብ የሳበው የሊዮኔል ሜሲ እና የኪሊያን ምባፔ ፍጥጫ ነው።የ35 ዓመቱ አርጀንቲናዊ ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ የዘንድሮውን ጨምሮ በአምስት የዓለም ዋንጫዎች 25 ጨዋታዎችን በማድረግ 11 ግቦችን አስቆጥሯል።

በ22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በስድስት ጨዋታ አምስት ግቦችን አስቆጥሯል። ሶስት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቿችቶ አቀብሏል።

ሜሲ ለአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን እስከ አሁን ባደረጋቸው 171 ጨዋታዎች 96 ግቦችን በማስቆጠር የአገሩ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ነው።

የ23 ዓመቱ ፈረንሳዊው ወጣት ኮከብ ኪሊያን ምባፔ የዘንድሮውን ጨምሮ በሁለት ዓለም ዋንጫዎች ላይ 13 ጨዋታዎችን አደርጎ ዘጠኝ ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።

በዘንድሮው ዓለም ዋንጫ አምስት ግቦችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ ከሊዮኔል ሜሲ የውድድሩን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት እየመራ ነው።

ለፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን እስከ አሁን 65 ጨዋታዎች አድርጎ 33 ግቦችን አስስቆጥሯል።

የመጨረሻው ዓለም ዋንጫ ተሳትፎውን የሚያደርገው ሊዮኔል ሜሲ በእግር ኳስ ሕይወቱ የሚመኘውን ትልቁን ክብር ያገኝ ይሆን? ወይስ ከዓለም ዋንጫው ፍጻሜ ሁለት ቀን በኋላ 24 ዓመቱን የሚደፍነው ኪሊያን ምባፔ ለሁለተኛ ዋንጫውን ያነሳል? ተጠባቂው ጨዋታ ምላሽ ይሰጣል።

የ41 ዓመቱ ፖላንዳዊ ሲሞን ማርሲኒያክ በከፍተኛ ጉጉት የሚጠበቀውን የፍጻሜ ጨዋታ የመሐል ሜዳ አለቃ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም