ተንቀሳቃሽ ንብረትን ዋስትና በማስያዝ የብድር አገልግሎት ማግኘት የሚያስችለው አዋጅ በቅርቡ ይፋ ይደረጋል - ኢዜአ አማርኛ
ተንቀሳቃሽ ንብረትን ዋስትና በማስያዝ የብድር አገልግሎት ማግኘት የሚያስችለው አዋጅ በቅርቡ ይፋ ይደረጋል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 9/2015 ተንቀሳቃሽ ንብረትን ዋስትና በማስያዝ የብድር አገልግሎት ማግኘት የሚያስችለው አዋጅ በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ ገለጹ።
የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር እና የገቢዎች ሚኒስቴር ከክልል የፕላን፣ የገንዘብና የገቢ ቢሮዎች ጋር የሚደረገው የምክክር መድረክ ዛሬም በአርባ ምንጭ ከተማ ቀጥሎ እየተካሄደ ነው።
በዚሁ ወቅት የፋይናንስ ተደራሽነትን እና ተንቀሳቃሽ ንብረትን በዋስትና በማስያዝ የብድር አገልግሎት ማግኘት የሚያስችለውን አዋጅ በማስመልከት ገለጻ ያደረጉት የብሔራዊ ባንክ ገዢው አዋጁ በተለይም ገጠራማውን የአገሪቱ አካባቢ ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ባንኮች እስከአሁን ከ330ሺ ለማይበልጡ ስዎች ብቻ ብድር መስጠታቸውን ገልጸዋል።
በተያያዘ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ከ6 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ብድር መስጠታቸውን ገልጸዋል።
በአገሪቷ ካሉት ዜጎች አንጻር ብድር የወሰዱ ዜጎች እጅግ አነስተኛ መሆናቸውን አንስተዋል።
ለዚህም የብድር ዋስትና ቋሚ ንብረት ላይ ትኩረት በማድረጉ ነው ብለዋል።
አሁን ላይ ይህን ችግር ለመፍታት ተንቀሳቃሽ ንብረትን በዋስትና በማስያዝ የብድር አገልግሎት የሚሰጥበት አዋጅን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁን ነው የጠቆሙት።
በዚህም በተለይ አርብቶ አደሩ እና አርሶ አደሩ እንስሳትን፣ ግመሎችን ፣ የግል ደኖችን፣ የመሬት መጠቀሚያ ደብተሮችን እና የመሬት መብትን በማስያዝ እና በሌሎችም ብድር ማግኘት የሚችል መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህ አዋጅም በቅርቡ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ይፋ እንደሚደረግም ገልጸዋል።
ይህ አዋጅም ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አንጻር ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑንም ተናግረዋል።
በየአካባቢው የሚገኙ የባንክ ቅርንጫፎችና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትም እንዲዘጋጁ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በምክክር መድረኩ ላይ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ፣ የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ፣ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እርስቱ ይርዳው እና ሌሎችም ከፍተኛ የፌደራል እና የክልሎች የሥራ ኃላፊዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።