የህዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ ልማት አጋዥነት ባሻገር የአካባቢያዊና ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ቅንጅት ምልክት ተደርጎ መወሰድ እንዳለበት ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ ልማት አጋዥነት ባሻገር የአካባቢያዊና ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ቅንጅት ምልክት ተደርጎ መወሰድ እንዳለበት ተጠቆመ
አዳማ (ኢዜአ ) ታህሳስ 08/2015 ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት አጋዥነት ባሻገር የአካባቢያዊና ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ቅንጅት ምልክት ተደርጎ መወሰድ እንዳለበት ተጠቆመ።
ለግድቡ ግንባታ ሕዝቡ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሀብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብረሃ አዱኛ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ለግድቡ ግንባታ ትኩረት በመስጠት ቀን ከሌት ርብርብ እየተደረገ ነው።
የግድቡ ግንባታ የኢትዮጵያውያን የአንድነት ምልክት መሆኑን ጠቅሰው፤ ግድቡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከውስጥም ከውጭም አንድ ያደረገ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች ጉዳዮች አማካሪ አምባሳደር ኢብራሂም እንዲሪስ በበኩላቸው፤ የግድቡ ግንባታን ከማፋጠን በተጓዳኝ ግድቡ የህልውና ጉዳይ መሆኑን የሚሳይ የዲፕሎማሲ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ስለ ግድቡ እውነታን ለዓለም በማሳወቅ አንጻር የምሁራን ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ምሁራንን ያሳተፈ ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑንም አስታውቀዋል።
''በአባይ ተፋሰስ ውስጥ ያለው የውሃ ሀብት 70 በመቶ ወደ ውጭ የሚሄድ ነው'' ያሉት አምባሳደር ኢብራሂም ፤የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችና ሀብት ልማት መብት ለማስከበር የሚያስችል የምሁራንና የዲፕሎማሲ አቅም መገንባት አለብን ብለዋል።
የህዳሴ ግድቡን ጨምሮ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ በመስራት ሀገራዊ ጥቅማችንን ማስጠበቅ አለብን ያሉት ደግሞ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ምህንድስና መምህር ዶክተር መኮንን አያና ናቸው።
የህዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት አጋዥነት ባሻገር የአካባቢያዊና ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ቅንጅት ምልክት ተደርጎ መወሰድ እንዳለበት ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ለኬንያ፣ ሱዳን፣ ጅቡቲና ደቡብ ሱዳን ሃይል እያቀረበችና ለሌሎችም ተደራሽ ለማድረግ አቅዳ እየሰራች መሆኑ አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ግድቡ ለአሁኑ ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ትውልድ የሚገነባ በመሆኑ ግንባታው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ዜጎች እያደረጉት ያለውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍና ርብርብ አጠናክሮ በማስቀጠል ግንባታውን ማጠናቀቅ አለብን ብለዋል።
በተለይ ስለ አባይና ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት የሚሰሩበትን መሰረት የሌለውን የፕሮፓጋንዳ ስራ ማክሸፍ የሚችል የኮሙዩኒኬሽንና የውሃ ዲፕሎማሲ ስራ ላይ ዩኒቨርሲቲዎችና የዘርፉ ምሁራን ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባም ጠቁመዋል።