የጥራት ደረጃቸውን ያልጠበቁ የምግብና የመድሃኒት ምርቶች ወደ አገር እንዳይገቡ በማድረግ በኩል ውጤታማ ስራ ተሰርቷል - ኢዜአ አማርኛ
የጥራት ደረጃቸውን ያልጠበቁ የምግብና የመድሃኒት ምርቶች ወደ አገር እንዳይገቡ በማድረግ በኩል ውጤታማ ስራ ተሰርቷል
አዳማ (አዲስ) ታህሳስ 08 ቀን 2015 ባለፉት አምስት ወራት የጥራት ደረጃቸውን ያልጠበቁ የምግብና የመድሃኒት ምርቶች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ በመቆጣጠር ውጤታማ ስራ ማከናወኑን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ገለጸ።
ባለስልጣኑ ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓት እውን ለማድረግና በተቋሙ የሪፎርም ስራዎች ዙሪያ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላትና አመራሮች ጋር እየመከረ ይገኛል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ተቋሙ የጥራት መሰረተ ልማት ዝርጋታዎችና ሪፎርም ላይ በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
ደህንነታቸው ያልተረጋገጠ፣ የተጭበረበረና የተመረቱበት ሀገርና ጊዜ በውል የማይታወቅ መድኃኒቶች ላይ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
'በቀጣይም ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓት ለመዘርጋትና የቁጥጥር ደረጃቸውን ለማሳደግ ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
የምክክር መድረኩ የተዘጋጀውም የቀጣይ 10 ዓመት ስትራቴጂ፣ ህገ-ወጥ ምግብና መድኃኒት ዝውውር ቁጥጥር እንዲሁም የተቋሙ ሪፎርም ያለበት ደረጃ ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ያለመ ነው ብለዋል።
በባለስልጣኑ የዕቅድና ፕሮጀክት ዳይሬክተር አቶ አብዮት አስጨናቂ በበኩላቸው፤ ባለፉት አምስት ወራት ለህብረተሰቡ ጤና ጠንቅ የሆኑ ከፍተኛ መጠን ያላቸው ምግቦች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ በመቆጣጠር ውጤታማ ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ መድኃኒቶች፣ የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችና የመዋቢያ ምርቶች ማስወገድ መቻሉን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በሀገር ውስጥ የተመረቱ ጨው፣ ዘይት፣ አቼቶ፣ በአድ ነገሮች የተቀላቀለባቸው የበርበሬ፣ ቅቤና የማር ምርቶች መወገዳቸውን ጠቅሰዋል።
104 የሚሆኑ መድኃኒትና የህክምና መሳሪያ አስመጪዎችና አካፋፋይ ተቋማት ላይ ከጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ጀምሮ እገዳና ፍቃድ የመሰረዝ እርምጃ የተወሰደባቸው መሆኑንም ነው ያመለከቱት።