ቀጥታ፡

መንግሥት የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው--የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 8/2015 መንግሥት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የገባቸውን ቃሎች ተግባራዊ በማድረግ ረገድ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለፀ።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት መንግሥት የገባቸውን ቃሎች ተግባራዊ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሁሉም የየብስ መተላለፊያዎች ወደ ትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ አኳያ እስከ ታህሳስ 5 ቀን  2015 ዓ.ም አልሚ ምግብን ጨምሮ ከ93 ሺህ በላይ ሜትሪክ ቶን ምግብ- ነክ ድጋፎች ወደ ትግራይ ክልል ተጓጉዟል ነው ያሉት፡፡

ከ8 ሺህ ቶን በላይ ምግብ-ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች እና ከ833 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ መጓጓዙንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በመንግሥት በኩል ዋጋቸው 78 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር የሚያወጡ መድኃኒቶች፣ በአጋር ድርጅቶች በኩል ደግሞ 158 ሜትሪክ ቶን ለተለያዩ ሕክምናዎች የሚያገለግሉ መድሃኒቶች ተደራሽ መሆናቸውንም እንዲሁ፡፡

መልሶ ግንባታን በተመለከተ በኤሌክትሪክ፣ በቴሌኮም፣ በመንገድ እንዲሁም በጤና ዘርፍ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታዋ አያይዘውም የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የአሜሪካ ቆይታ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩና የልዑካን ቡድናቸው በአሜሪካ የተሳካ ቆይታ አድርገው ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውንም ነው የገለጹት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ-አፍሪካ ጉባዔ ተገኝተው ከጉባዔው ጎን ለጎን ከአሜሪካ መሪዎችና ባለሥልጣናት ጋር ውጤታማ ውይይቶችን ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በውይይቱ የኢትዮጵያ መንግሥት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ሰላምን ለማምጣት የወሰደው እርምጃ እውቅና ያገኘበት መሆኑንም አመላክተዋል።

በተለይ ለስምምነቱ ትግበራ ያሳየው ቁርጠኝነት አድናቆት እንደተቸረው እንዲሁ።

አሜሪካና ኢትዮጵያ በጋራ የሚሰሯቸውን የልማትና ሌሎች በርካታ ጉዳዮችን አጠናክረው ለማስቀጠል መስማማታቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

በሌላ መልኩ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ልማት ላስመዘገበችው ስኬትና ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ለማስፋት ለምታደርገው ጥረት እውቅና እንደተሰጠውም አንስተዋል፡፡

በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም  ከዓለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍ የተገኘበት እንዲሁም ለቀጣይ ድጋፎችም መሰረት የተጣለበት ቆይታ መሆኑን አመላክተዋል።

በአጠቃላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሜሪካ ቆይታ በዲፕሎማሲ መስክ ስኬት የተመዘገበበት እና ኢትዮጵያ ያላትን የዲፕሎማሲ አቅም ከፍ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም