‘ለዘላቂ ሰላምና ልማት እንሩጥ’ በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የጎዳና ላይ ሩጫ በደቡብ ሱዳን ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
‘ለዘላቂ ሰላምና ልማት እንሩጥ’ በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የጎዳና ላይ ሩጫ በደቡብ ሱዳን ተካሄደ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 8/2015 ‘ለዘላቂ ሰላምና ልማት እንሩጥ’ በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የጎዳና ላይ ሩጫ በደቡብ ሱዳን ዛሬ ተካሄዷል።
‘ታላቁ የደቡብ ሱዳን ሩጫ’ የሚል ስያሜ በተሰጠው ውድድር ደቡብ ሱዳናውያን፣ የኬንያ፣ የኢትዮጵያ፣ የዩጋንዳና ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ አገራት መሳተፋቸውን በጁባ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያወጣው መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታዎች አሸንፈዋል።
አትሌት አበበ ነገዎ በወንዶች እንዲሁም አትሌት ዓለምአዲስ እያዩ በሴቶች ያሸነፉ አትሌቶች ናቸው።
በሁለቱም ጾታዎች በቅደም ተከተል የኬንያ እና ዩጋንዳ አትሌቶች ሁለተኛና ሶስተኛ ወጥተዋል።
በጎዳና ላይ ሩጫው የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንቶች ታባን ዴን ጋይ እና ሬቤካ ንያንዴንግ ዲ ማቢዮር እንዲሁም በጁባ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ ማርቆስ ተክሌ (ዶ/ር) እና የኤምባሲው ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል።
በደቡብ ሱዳን የሚገኙት የኢትዮጵያ ባለሀብት እና የታላቁ የደቡብ ሱዳን ሩጫ መስራች አቶ አይሸሹም ተካ ውድድሩ በየዓመቱ እየተካሄደ እንደሚገኝና ዋና ዓላማውም በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላምና እርቅ እንዲመጣ እየተደረገ ያለውን ጥረት ማስተዋወቅ ነው ብለዋል።
የታላቁ የደቡብ ሱዳን ሩጫ ከእ.አ.አ 2017 አንስቶ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያወጣው መረጃ ያመለክታል።