ቀጥታ፡

በሁለት ዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታዎች ለሁለት አገራት የተጫወተው ሉዊስ ፍሊፔ ሞንቲ

(በሙሴ መለስ)

ኡራጓይ እ.አ.አ 1930 ራሷ ያዘጋጀችውን የመጀመሪያ የፊፋ ዓለም ዋንጫ አነሳች። እ.አ.አ 1934 የተካሄደውን ሁለተኛውን የፊፋ ዓለም ዋንጫ ጣልያን አዘጋጅታ ራሷ ወሰደችው።

ሁለቱ የዓለም ዋንጫዎች ታዋቂው የእግር ኳስ ጸሐፊ ጋሪ ታከር እ.አ.አ ሰኔ 6 2018 በብሪታኒያው ዕለታዊ ጋዜጣ ዘ ጋርዲያን ስለ አንድ ተጫዋች ላጸፈው ሐተታ መነሻ ሆኖታል።

ተጫዋቹ ሉዊስ ፍሊፔ ሞንቲ ይባላል።

ጋሪ ታከር ‘Luis Monti: the man who played in two World Cup finals for two countries’ በሚል ርዕስ ባሰፈረው ጽሁፍ ሐተታውን ይጀምራል።

በሁለት ተከታታይ ዓለም ዋንጫዎች ፍጻሜ የደረሱ አገራት እነማን ናቸው? ጣልያን፣ብራዚል፣ አርጀንቲና እና ኔዘርላንድስ ይህን ማሳካት ችለዋል።

ጀርመን(በወቅቱ መጠሪያዋ ምዕራብ ጀርመን) እ.አ.አ 1982፣1986 እና 1990 በተካሄዱ ሶስት ተከታታይ ዓለም ዋንጫዎች ፍጻሜ በመድረስ ታሪክ ሰርታለች።

የተወሰኑ ተጫዋቾች በሁለት ተከታታይ ዓለም ዋንጫዎች መሳተፍ ቢችሉም ሉዊስ ፍሊፕ ሞንቲ ከነዚህ ተጫዋቾች የተለየ ነው ይላል ጋሪ ታከር።

ሞንቲ እ.አ.አ በ1930 ኡራጓይ ባስተናገደችው የመጀመሪያ ዓለም ዋንጫ አርጀንቲናን ወክሎ የተጫወተ ሲሆን አርጀንቲና በፍጻሜው ጨዋታ በአዘጋጇ አገር 4 ለ 2 ተሸንፋለች።

እ.አ.አ 1934 በተካሄደው ሁለተኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ አዘጋጇ አገር ጣልያን በወቅቱ አጠራሯ ቼኮዝሎቫኪያን(አሁን ቼክ ሪፐብሊክ እና ስሎቫኪያ በሚል ለሁለት ተከፍላለች)  2 ለ 1 በማሸነፍ ዋንጫውን ስታነሳ ሉዊስ ሞንቲ የቡድኑ አባል ነበር።

ሉዊስ ፍሊፔ ሞንቲ እንዴት በሁለት ዓለም ዋንጫዎች ለሁለት አገራት ሊጫወት ቻለ? የሚለው ጉዳይ የአብዛኞቹ ጥያቄ ነው።

ጋሪ ታከር ጽሁፉን ይቀጥላል።

ሉዊስ ፊሊፔ ሞንቲ እ.አ.አ ግንቦት 15 1901 በአርጀንቲና ቦነስ አይረስ ተወለደ።

የእግር ኳስ ሕይወቱን በአርጀንቲናው አትሌቲኮ ሁራካን ክለብ የጀመረ ሲሆን ክለቡን በተቀላቀለበት ዓመት የሊጉ አሸናፊ መሆን ቻለ። በታዋቂው ቦካ ጁኒየርስ ክለብ አጭር ቆይታ ካደረገ በኋላ ወደ ሌላኛው የአርጀንቲና ክለብ ሳንሎሬንዞ አመራ።

ጋሪ ታከር ሳንሎሬንዞ ሉዊስ ሞንቲ ስሙን እንዲታወቅ አድርጎታል ይላል። በክለቡ በነበረው ቆይታ ኳስ በማስጣል ብቃቱ እና ጥንካሬው እንዲሁም የቴክኒክ ክህሎትና ብስለቱ በላቲን ‘Doble Ancho’ በእንግሊዘኛው ‘Double wide’ የሚል ስያሜ አሰጥቶታል።

ሞንቲ የሜዳውን ክፍል በማካለል የሚያደርገው እንቅስቃሴ ዓለቱና የማይበገረው የሚል ውዳሴን አስገኝቶለታል።

ሉዊስ ፍሊፔ ሞንቲ እ.አ.አ 1929፣1924 እና 1927 ከሳንሎሎሬንዞ ጋር የአርጀንቲና ሊግ ዋንጫን አነሳ። በክለቡ ያሳየው ብቃት እ.አ.አ 1927 ፔሩ ባሰናዳችው 11ኛው የደቡብ አሜሪካ የእግር ኳስ ሻምፒዮና ለአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን እንዲጫወት ጥሪ ቀረበለት።

አርጀንቲና በሻምፒዮናው የፍጻሜ ጨዋታ ፔሩን 5 ለ 1 በመርታት ዋንጫውን ስታነሳ ሞንቲ የቡድኑ አባል ነበር። ሞንቲ እ.አ.አ 1928 በኔዘርላንድስ አምስተርዳም በተካሄደው ዘጠነኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በእግር ኳስ ውድድር ከአርጀንቲና ጋር የብር ሜዳሊያ አግኝቷል።

በፍጻሜው ጨዋታ አርጀንቲና በኡራጓይ 2 ለ 1 ስትሸንፍ ሉዊስ ሞንቲ ብቸኛዋን ግብ አስቆጥሯል። እ.አ.አ በ1930 ኡራጓይ ባዘጋጀችው የመጀመሪያው ዓለም ዋንጫ ሞንቲ በአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን ተካተተ።

አርጀንቲና እ.አ.አ ሐምሌ 15/1930 በስታዲዮ ግራን ፓርኬ ባደረገቸው የምድቧ የመጀመሪያ ጨዋታ ፈረንሳይን 1 ለ 0 ስታሸንፍ የማሸነፊያዋን ግብ በ81ኛው ደቂቃ በቅጣት ምት ያስቆጠረው ሉዊስ ፊሊፔ ሞንቲ ነበር።

አርጀንቲና በምድብ አንድ ሜክሲኮን 6 ለ 3 በመርታት እንዲሁም ቺሊን 3 ለ 1 በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍጻሜ አልፋለች።

አርጀንቲና በግማሽ ፍጻሜው አሜሪካን 6 ለ 1 ስትረታ የመጀመሪያዋን ግብ ያስቆጠረው ሉዊስ ፊሊፔ ሞንቲ ነበር።

አርጀንቲና በፍጻሜው በወቅቱ አጠራሯ ዩጎዝላቪያ(አሁን ፈርሳ ወደ ተለያዩ አገራት ተከፋፍላለች) 6 ለ 1 ካሸነፈችው ኡራጓይ ጋር ቀረበች።

በሞንቴቪዲዮ ከተካሄደው የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ በፊት ሞንቲ  ጉዳት አጋጥሞት ነበር። ይሄም በጨዋታው የሚጠበቅበትን ብቃት እንዳያሳይ አድርጎታል የሚሉ ወሬዎች መናፈስ ጀመሩ።

ከእረፍት በፊት 2 ለ 1 እየመራች የነበረችው አርጀንቲና ከእረፍት መልስ ሶስት ግብ ተቆጥሮባት 4 ለ 2 ተሸነፈች።

ከረጅም ዓመታት በኋላ አያቱ ሎሬና ሞንቲ በሰጡት አስተያያት ሞንቲ በጨዋታው የሚጠበቅበትን ብቃት ያላሳየው ጉዳት ብቻ ስላጋጠመው እንዳልሆነ መግለጻቸውን ጋሪ ታከር በጽሁፉ አስፍሯል።

“አርጀንቲና ጨዋታውን 2 ለ 1 እየመራች እረፍት ወጣች፤ የማላውቃቸው ሰዎች አርጀንቲና ካልተሸነፈች ባለቤቴንና አክስቴን እንደሚገላት ዛቱ” ሲሉ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳሉ።

ሎሮና ሞንቲ ከቤተሰቦቼ ውጪ ሌሎች የአርጀንቲና ተጫዋቾች ማስፈራሪያ እንደደረሳቸውና የልጅ ልጃቸው ሉዊስ ሞንቲ ዛቻ እንደመጠባት ገልጸዋል።

በስተመጨረሻም ኡራጓይ በ1930 ያዘጋጀችውን የዓለም ዋንጫ አነሳች። ሞንቲም የእግር ኳስ ቆይታውን በሳንሎሬንዞ ክለብ ቀጠለ።

ነገር ግን ሞንቲ ለአርጀንቲናው ክለብ ሲጫወት በነበረበት ወቅት ሊያዩት የመጡት ሁለት ጣልያናውያን የሕይወቱ ለውጥ መታጠፊያ ሆነለት ይላል ጋሪ ታከር። ሊያቱት የመጡት ጣልያናውያን በቅርቡ ከጣልያን ክለብ የዝውውር ጥያቄ እንደሚቀርብለት ነገሩት። ጥያቄውን ከተቀበለ ወርሃዊ ክፍያው ወደ አምስት ሺህ ዶላር ከፍ እንደሚልና ቤት እና መኪና እንደሚሰጠው ቃል ተገባለት።

ሁለቱ ሰዎች ለሞንቲ ጥያቄውን እንዲያቀርቡ የላኩት የወቅቱ የጣልያን መሪ ቤኒቶ ሞሶሎኒ ናቸው። እ.አ.አ በ1934 ጣልያን የዓለም ዋንጫውን እንድታዘጋጅ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር(ፊፋ) ተመረጠች።

ጋሪ ታከር ዓለም ዋንጫው ቤኒቶ ሞሶሎኒ ጣልያን በውድድሩ ከሌሎች የእግር ኳስ ኃያላን ጋር ተወዳድራ ቀዳሚውን ስፍራ እንድትይዝ ፍላጎት እንደነበራቸው ገልጿል።

የሉዊስ ሞንቲ ቅደመ አያቶች በሰሜን ጣልያን በምትገኘው ኢሚሊያ-ሮማግና የተወለዱ ናቸው። ለሞንቲ ጥያቄውን ያቀረበው ክለብ ላዚዮ ሳይሆን ሞሶሎኒ የሚደግፉት ጁቬንቱስ ነበር።

የጣልያን ሊራ ያማለለው ሉዊስ ሞንቲ ወደ ቱሪን በማምራት እ.አ.አ 1931 ለጁቬንቱስ ፈረመ። የጣልያንን ዜግነት አገኘ ሲል ጋሪ ታከር ገልጿል።

ሉዊስ ሞንቲ ለአርጅነቲና ብሔራዊ ቡድን በ16 ጨዋታዎች አምስት ግቦችን አሳርፏል። ሞንቲ ‘ላ አሊቤሴሌስቴ’(ነጭ እና ሰማያዊ የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን ቅጽል ስም ነው) ወደ ‘ግሊ አዙሪ’ (ሰማያዊዎቹ) ጣልያን ሄደ።

እ.አ.አ 1931 ጁቬንቱስን የተቀላቀለው ሉዊስ ሞንቲ በቱሪኑ ክለብ በነበረው የዘጠኝ ዓመት ቆይታው በተከላካይ አማካይ መስመር በነበረው ሚና ክለቡ አራት የስኬዴቶውን ዋንጫ እንዲያነሳ አስተዋጽኦ አድርጓል። ክለቡን በአምበልነትም አገልግሏል።

ከ200 በላይ ጨዋታዎችን አድርጎ 20 ግቦችን ለአሮጊቶቹ(የጁቬንቱስ ቅጽል ስም) አስቆጥሯል።

ጋሪ ታከር ይቀጥላል።

ሉዊስ ፊሊፔ ሞንቲ ወደ ጣልያን የመጣው በጁቬንቱስ ብቻ ለመጫወት አይደለም፤ በጣልያን መሬት በሚካሄደው ሁለተኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ዋንጫው እዛው እንዲቀር ብሔራዊ ቡድኑን ለመርዳትም ጭምር ነው ብሏል።

እ.አ.አ ግንቦት 27 1934 ጣልያን ናዚዮናሌ ስታዲየም የሁለተኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ መክፈቻ ጨዋታ ተካሄደ።

ጣልያን አሜሪካን 7 ለ 1 በመረምረም በፍጹም የበላይነት አሸንፋ ለሩብ ፍጻሜ አለፈች። ሉዊስ ሞንቲ በጨዋታው ባይሰለፍም የጣልያን ብሔራዊ ቡድን አባል ነበር።

ጣልያን ባሸነፈችበት ተመሳሳይ ቀን በመጀመሪያው ዓለም ዋንጫ የወከላት አርጀንቲና በቦሎኛ ከተማ በተደረገ ጨዋታ በስዊድን 3 ለ 2 ተሸንፋ ከውድድሩ ውጪ ሆነች።

ጣልያን አሜሪካን ማሸነፏን ተከትሎ በሩብ ፍጻሜው ከስፔን ጋር ተገናኘች። እ.አ.አ ግንቦት 31 1934 ያደረጉት ጨዋታ 1 ለ 1 ተጠናቀቀ።

አሸናፊውን ለመለየት በወቅቱ የነበረው የፊፋ አሰራር በቀጣዩ ቀን ሁለተኛ ጨዋታ ማድረግ ነው።

እ.አ.አ ሰኔ 1 1934 በተደረገው ጨዋታ ጣልያን ጁሴፔ ሜኤዛ 11ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ግብ ስፔንን 1 ለ 0 በማሸነፍ በደርሶ መልስ ውጤት ወደ ግማሽ ፍጻሜው አለፈች።

ጋሪ ታገር ሁለቱ ጨዋታዎች ሽኩቻ የበዛባቸው፣ኃይል የተቀላቀለባቸው እና ፍትጊያ የነበረባቸውው እንደነበሩ ገልጿል።

ጣልያን በግማሽ ፍጻሜ በሳን ሲሮ ስታዲየም ከኦስትሪያ ጋር ያደረገችውን ጨዋታ በኤኔሪኬ ጉያታ ግብ 1 ለ 0 አሸነፈች።

የኦስትሪያ አይን ሳቢ ጨዋታ በጨዋታው መሐል በሳን ሲሮ ጥሎ በነበረው ዝናብ እክል ገጠመው። ይሁንና በጨዋታው ለጣልያን በተከላካይ አማካይ ስፍራ የተጫወተው ሉዊስ ሞንቲ የኦስትሪያውን አጥቂ ማቲያስ ሲንዴላርን እንቅስቃሴ በመግታት ፍጻሜ መድረስ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ጋሪ ታከር ገልጿል።

በሁለቱ አገራት የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ጁሴፔ ሜኤዛ የኦስትሪያዊውን ግብ ጠባቂ ፍሬድሪች ፍራንዝል የያዘውን ኳስ በትከሻው በመግጭት አስጣለው። ኤኔሪኬ ጉያታ ግቡን አስቆጠረ። የዕለቱ የመሐል ዳኛ ስዊዲናዊው ኢቫን ኢክሊንድ ጎሎን ያጸደቁበት መንገድ በኦስትሪያ ተጫዋቾች ቁጣን የቀሰቀሰና ውዝግብ የፈጠረ ነበር።

ግቡን ያስቆጠረው ኤነሪኬ ጉያታ እንደ ሞንቲ በአርጀንቲና የተወለደ ተጫዋች ነው።

ስዊዲናዊው ኢቫን ኢክሊንድ በግቡ ብቻ ሳይሆን በጨዋታው እንቅስቃሴ ውሳኔያቸው ጣልያንን ደግፈዋል የሚል ትችት ቢቀርብባቸውም ፊፋ የፍጻሜውን ጨዋታ አንዲመሩ መረጣቸው።

እ.አ.አ ሰኔ 10 1934 ሮም ናዚዮናሌ ስታዲይም ጣልያን ከቼኮዝሎቫኪያ(አሁን ቼክ ሪፐብሊክ እና ስሎቫኪያ በሚል ለሁለት ተከፍላለች) የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ጨዋታ የሚካሄድበት ቀን ነው።

ከጨዋታው አንድ ቀን በፊት ጣልያኖች ወዳረፉበት ክፍል በቴሌግራም አንድ መልዕክት ለአሰልጣኑ ቪቶሪዮ ፖዞ እና ተጫዋቾቹ ደረሰ ይላል ጋሪ ታከር። “አሸንፉ ካለሸነፋችሁ አደጋ ላይ ትወድቃላችሁ” የሚል እንደነበር ገልጻል።

የቴሌግራሙ መልዕክት ከጣልያኑ መሪ ቤኒቶ ሞሶሎኒ እንደመጣ ተነገረ። ለጣልያን ተጫዋቾች ጨዋታው በእግር ኳስ ትልቁን ከብር የሚያሰጥ መሆኑ ራሱ ጫና ቢኖረውም የሞሶሎኒ መልዕክት የጫናውን ግዝፈት ጨምሮታል ነው ያለው።

ቼኮዝሎቫኪያ(በወቅቱ አጠራሯ የተቀመጠ ነው) በግማሽ ፍጻሜው ጀርመንን(በወቅቱ ምዕራብ ጀርመን) 2 ለ 1 በማሸነፍ ለፍጻሜ ቀርባለች።

ቼኮዝሎቫኪያ ከፍፃሜው ጨዋታ በፊት ደካማ አቋም ነው ያላት ጨዋታውን ጣልያን በቀላሉ ታሸንፋለች የሚል ግምት ተሰጥቶት ነበር።

ይሁንና ጨዋታውን በጥሩ ሁኔታ በመጀመር የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን የሁለቱ ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ያለ ምንም ግብ አቻ ተጠናቀቀ።

በእረፍት ሌላ አጭር እና ግልጽ መልዕክት ከሞሶሊኒ ወደ ጣልያን መልበሻ ክፍል ከአሰልጣኙ ቪቶሪዮ ፖዞ ተላከ።

ሉዊስ ሞንቲ  በሁለቱ ዓለም ዋንጫዎች ተጻራሪ ስጋቶች በዚሁ መልኩ ይገልጸዋል።

“አያቴ ሎሬና በሁለት አገራት በዓለም ዋንጫው መጫዋቴ ስጋት ውስጥ አንደሚከተኝ ትነግሮኝ ነበር። በኡራጓይ ዓለም ዋንጫ አርጀንቲና ብታሸንፍ ጉዳት እንደሚደርስብኝ ነበር የተነገረኝ። በጣልያን ግን ከተሸንፍን አደጋ ውስጥ እንደምገባ ተረዳሁ እንግዳ ነገር ነው የሆነብኝ” ብሏል።

አንቶኒን ፑክ 71ኛው ደቂቃ ለቼኮዝሎቫኪያ ግብ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ አደረገ። በጣልያን ጨዋታዎች ላይ ጫናው ይበልጡኑ በረታ። ጂሪ ሶቦትካ የሳተው ባዶ ጎል እና ፍራንቲሴክ ስቮቦዳ የግብ አግዳሚ የመለሰበት አጋጣሚ ጣልያን ከተጨማሪ ስጋት ያተረፈና አዙሪዎቹ ጨዋታው ላይ እንዲቆዩ አድርጓል።

ጣልያን መሸነፏ እርግጥ ነበር ሲባል ራሚሞንዶ ኦርሲ በ81ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ አዙሪዎች አቻ ሆኑ በናዚዮናሌ ስታዲየም የነበረው ደጋፌ ስሜቱ ከጭንቀት ወደ ደስታ እንዲቀየር አደረገ። ጎሉ ሞሶሎኒን ጨምሮ ያስፈነጠዘ ነበር ይላል ጋሪ ታከር።

ጨዋታው ወደ ጭማሬ ሰአት አመራ። ጣልያን አገገመች የጨዋታ ብልጫም ወሰደች። 95ኛው ደቂቃ ላይ አንጄሎ ስካቪዮ ከጠባብ አንግል ያስቆጠራት ግብ ጣልያንን መሪ አደረገች። ስታዲየሙ በደስታ ተደበላለቀ።

ስዊዲናዊው ኢቫን ኢክሊንድ የጨዋታውን መጠናቀቅ የሚያስረውን ፊሽካ አሰሙ። ጣልያን በፊፋ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጁሌስ ሬሜት የተሰየመውን ዋንጫ አምበሉ ጂያንፒዬሮ ኮምቢ ተረከበ።

ሉዊስ ፍሊፔ ሞንቲ “ከጨዋታው በኋላ የፈለጋችሁትን መጠየቅ ትችላላችሁ ተባልን፤ገንዘብ ወርቅ ቤት መኪኖች ፤ ከድሉ በኋላ በጣልያን የተከበሩ የሰው ልጆች ሆንን” ሲል ገልጿል።

ጋሪ ታከር ሉዊስ ሞንቲ በሁለት ዓለም ዋንጫዎች ለሁለት አገራት በመጫወት የተለየ ታሪክ ማስመዘገቡን አውስቷል። ይሄ አስገራሚ ታሪክ ከዚህ በኋላ በሌሎች ዓለም ዋንጫዎች ይፈጠር ይሆን ወይ? ታከር የመቀየር እድሉ ጠባብ ነው ሲል ጽሁፉን ቋጭቷል።

ሉሲስ ፍሊፔ ሞንቲ ለጣልያን ብሔራዊ ቡድን 18 ጨዋታዎችን አድርጎ አንድ ግብ አስቆጥሯል።

ሞንቲ ከእግር ኳስ ከተገለለ በኋላ የጣልያኖቹን ክለቦች ጁቬንቱስ ፣አትላንታ ፣ትሪዬስቲና ፣ቫሬሴ፣ ቩጌቫኖ እና ፒሳ እንዲሁም የአርጀንቲናውን ሁራካን ክለብ አሰልጥኗል።

እ.አ.አ 1983 በ82 ዓመቱ ሕይወቱ አልፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም