ቀጥታ፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የአሜሪካ ቆይታ ኢትዮጵያ ያላትን የዲፕሎማሲ አቅም ከፍ ያደረገ ነው-የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 8/2015 የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የአሜሪካ ቆይታ ኢትዮጵያ ያላትን የዲፕሎማሲ አቅም ከፍ ያደረገ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለመገናኛ ብዙሀን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይና ሉዑካን ቡድናቸው በአሜሪካ የተሳካ ቆይታ አድርገው ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ-አፍሪካ ጉባኤ ተገኝተው ከጉባኤው ጎን ለጎን ከአሜሪካ መሪዎች ጋር ውጤታማ ውይይቶች ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በውይይቱ የኢትዮጵያ መንግስት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ሰላምን ለማምጣት የወሰደው እርምጃ እውቅና ያገኘበት መሆኑንም አመልክተዋል።

በተለይ ለስምምነቱ ትግበራ መንግስት ያሳየው ቁርጠኝነት አድናቆት እንደተቸረውም እንዲሁ።

አሜሪካና ኢትዮጵያ በጋራ የሚሰሯቸውን የልማትና ሌሎች በርካታ ጉዳዮችን አጠናክረው ለማስቀጠል መስማማታቸውንና  ሁለትዮሽ ግንኙነቱን ወደ ቀደመ መልኩ ለመመለስ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ሚሊየኖችን አስተባብራ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን መትከል መቻሏና ወደ ሌሎች አፍሪካ ሀገራት ለማስፋት የምታደርገው ጥረት እውቅና የተሰጠበት መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታዋ አክለዋል።

ኢትዮጵያ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ለመልሶ ግንባታ የምታደርገውን ጥረት የአለም አቀፍ ድጋፎች የተገኘበት እንዲሁም ለቀጣይ ድጋፎችም መሰረት የተጣለበት ቆይታ መሆኑን አመላክተዋል።

በአጠቃላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሜሪካ ቆይታ በዲፕሎማሲው መስክ ስኬት የተመዘገበበት እና ኢትዮጵያ ያላትን የዲፕሎማሲ አቅም ከፍ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም