አገሪቱ ተግባራዊ የምታደርገው አካታች አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች አዎንታዊ ለውጦች እያስመዘገበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አገሪቱ ተግባራዊ የምታደርገው አካታች አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች አዎንታዊ ለውጦች እያስመዘገበ ነው
አዲስ አበባ /ኢዜአ/ ታህሳስ 7/2015 ኢትዮጵያ ተግባራዊ የምታደርገው አካታች አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች አዎንታዊ ለውጦች እያስመዘገበ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ ገለጹ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት መርሃ ግብር ዓመታዊ ጉባኤውን በአዲስ አበባ አድርጓል።
በመድረኩም ኢትዮጵያ" በ2030 ወደ ላቀ ሁሉን አቀፍ ማሻሻሎች በመሻገር ለመጪው ትውልድ አዲስ ሪፎርም መንገድ ይፈጠር ይሆን? በሚል ሃሳብ ውይይት ተደርጓል።
የፕላንና ልማት ሚስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ በዚሁ ወቅት አጠቃላይ የኢትዮጵያን አሁናዊ የኢኮኖሚና ሁሉን አቀፍ የልማት ስኬቶችና ተግዳሮቶች አብራርተዋል።
በዚህም መንግሥት የአስር ዓመት መሪ የልማት እቅድ አውጥቶ በግብርና፣ በኢቨስትመንት፣ በኢንደስትሪ በንግድና ሌሎች የልማት መስክ ሰፊ ሥራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።
በተጓዳኝም በትምህርት፣ በጤና፣ በአይሲቲ ቴክኖሌጂና ኢኖቬሽንና በሌሎችም ወሳኝ የምጣኔ ሃብት ዘርፎች ላይ አገሪቷ ዘርፈ ብዙ ለውጦችን እያስመዘገበች መሆኑን ነው ያስረዱት።
በተለይም ደግሞ እ.አ.አ በ2019 ተግባራዊ መሆን የጀመረው አካታች አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ተግባራዊ የሆነ እምርታዊ ለውጦችን እያስመዘገበ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ሂደቱ በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት፣ የኮቪድ 19 ተጽእኖ ሥር የቆዩ ቢሆንም በተለይ በኢኮኖሚው ዘርፍ ጠንካራ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ነገር ግን በወቅቱ ያጋጠመው ቀውስ የአገሪቷን ምጣኔ ሃብታዊ እድገት መፈተኑን ጠቁመዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተነሳሽነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄም ትልቅ ውጤት እያስመዘገበ ያለ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
በቀጣይም ኢትዮጵያ የተያያዘችውን የእድገት አቅጣጫ በማስቀጠል አገራዊ የልማት ግቦችን ለማሳካት ትሰራለች ነው ያሉት።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት መርሃ ግብር የኢትዮጵያ ተወካይ ቱሩሃን ሳልህ በበኩላቸው ተቋማቸው ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ ያጠናክራል ብለዋል።
ተቋሙ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያካሂደውን የልማት ፕሮጀክቶች በፋይናንስና በቴክኒክ ለመደገፍ በትኩረት እንደሚሰራ ነው የገለጹት።