ለህብረተሰብ ጤና ስጋት የሆኑ ጉዳዮችን ለመከላከል ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ይገባል---ኢንስቲትዩቱ - ኢዜአ አማርኛ
ለህብረተሰብ ጤና ስጋት የሆኑ ጉዳዮችን ለመከላከል ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ይገባል---ኢንስቲትዩቱ
ሐዋሳ (ኢዜአ) ታህሳስ 7/2015 በህብረተሰቡ ዘንድ የጤና ስጋት የሆኑ ችግሮችን ቀድሞ ለመከላከል የተቋማት ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
ብሔራዊ "የአንድ ጤና" ቀን ዛሬ በሃዋሳ ከተማ ሲከበር የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሃይሉ እንደገለጹት የአንድ ጤና ጥምረት የሰዎች፣ የአካባቢና የእንስሳትን ጤና ደህንነት በተቀናጀ መልኩ ለመከላከል የሚያስችል ነው፡፡
አብዛኞቹ ተላላፊ በሽታዎች ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ፣ ከአካባቢ ንጽህናና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ለህብረተሰቡ የጤና ስጋት የሆኑ ችግሮችን ቀድሞ ለመከላከል የተለያዩ ሴክተር ተቋማት ቅንጅታዊ ሥራ ይጠይቃል ብለዋል፡፡
ለዚህም ብሔራዊ የአንድ ጤና ጥምረት በሀገር አቀፍ ደረጃ ተቋቁሞ የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ነው ዶክተር መሳይ የገለጹት።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት ስጋት የሆኑ በሽታዎችን ለመከላከልና ቅኝት ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ የአተገባበር መመሪያዎች የተዘጋጁ ሲሆን ግንዛቤ መፍጠር የሚያስችሉ ማኑዋሎችም ተዘጋጅተው ሥራ ላይ እንዲውሉ ተደርጓል፡፡
በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በእንስሳትም ሆነ በሰው ላይ ከዚህ ቀደም ያልነበሩና ቀንሰው የነበሩ በሽታዎች በድጋሚ እየታዩ መሆኑን ጠቅሰው፣ "ልዩ ምርመራ የሚፈልጉ በሽታዎች ሲያጋጥሙ ከክልሎች ጋር በጋራ እየተሰራ ነው" ብለዋል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የህብረተሰብ ጤና አገልግሎት ዘርፍ ሃላፊው ዶክተር ሲሳይ ጌታቸው በበኩላቸው "በአንድ ጤና ጥምረት" አማካይነት በሰው፣ በአካባቢና በእንስሳት የሚከሰቱ በሽታዎች ላይ በተለያየ ጊዜ ቅኝት መደረጉን ገልጸዋል፡፡
የአንድ ጤና ጥምረቱ በህብረተሰቡ ስጋት ከሆኑ በሽታዎች መካከል የእብድ ውሻ በሽታን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2030 ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ግብ ጥሎ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም ባለፈው ዓመት በዘጠኝ ክልሎች በተመረጡ 13 ከተሞች ላይ በርካታ ውሾች እንዲከተቡ መደረጉን ጠቅሰዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ለተለያዩ በሽታዎች ምክንያት እየሆነ መምጣቱን የገለጹት ዶክተር ሲሳይ ኮቪድ 19፣ የኢቮላ ቫይረስ እና ሌሎች ከእንስሳት ጋር የተያያዙ በሽታዎችን ለመከላከል ቅንጅታዊ ሥራው ጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል።
"የሰው፣ የአካባቢንና እንስሳት ጤናን ለመጠበቅ በጥምረት እየሰራን ነው" ያሉት ደግሞ የፌደራል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ወይዘሮ ፍሬነሽ መኩሪያ ናቸው፡፡
በከተሞች የህዝብ ቁጥር መጨመር ለአየር ብክለት መንስኤ መሆኑን ጠቁመው፣ "አካባቢን አለመጠበቅ ለበርካታ ተላላፊ በሽታዎች መንስኤ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት ይገኛል" ብለዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ቅንጅታዊ አሰራሩን ማጠናከርና ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞን ማረጋገጥ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
የዓለም አቀፍ የጤና ደንብ የኢትዮጵያ ተጠሪና "የአንድ ጤና" አስተባባሪ ዶክተር ፈይሳ ረጋሳ በበኩላቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የጤና ስጋት የሆኑ ጉዳዮች በሰው፣ በእንስሳትና በአካባቢ መስተጋብር ውስጥ የሚከሰቱ ናቸው ብለዋል፡፡
"የጤና ጉዳይ በአንድ ተቋም ብቻ የሚሰራ ባለመሆኑ በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል" ያሉት አስተባባሪው፣ አራት ዓለም አቀፍ ተቋማትም በጋራ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ቅንጅታዊ ሥራው ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ድረስ የወረደ መሆኑን ጠቁመው፣ ለእዚህም የአምስት ዓመት ዕቅድ ወጥቶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ኮቪድ-19 እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ወረርሽኞች መበራከት ችግሩ እየጎላ ስለመምጣቱ ማሳያ በመሆናቸው ከዘመቻ ሥራዎች ይልቅ ቅድመ መከላከል ላይ መጠንከር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡
የ"አንድ ጤና" ሃሳብ በዓለም አቀፍ ደረጃ የህብረተሰብ ጤና ስጋት የሆኑ የጤና ችግሮችን ተቋሟት በተቀናጀ መንገድ እንዲከላከሉ ለማስቻል በ2003 የተመሰረተ ጥምረት ነው።
በመድረኩ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከአካባቢ ጥበቃና ሌሎች በጥምረት ከሚሰሩ ተቋማት የተወከሉ አካላት ተሳትፈዋል፡፡
በ"አንድ ጤና" ጥምረት አማካይነት የተከናወኑ ተግባራት በመድረኩ የተገመገሙ ሲሆን በቀጣይ ትኩረት በሚደረግባቸው ጉዳዮች ላይም ውይይት ተደርጓል፡፡