ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የስደተኞች ተፅዕኖ ምላሽ ፕሮጀክት በመተግበር ረገድ ውጤታማ ሰራ ማከናወኗ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የስደተኞች ተፅዕኖ ምላሽ ፕሮጀክት በመተግበር ረገድ ውጤታማ ሰራ ማከናወኗ ተገለጸ
ጋምቤላ (ኢዜአ) ታህሳስ 7 ቀን 2015 ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የስደተኞች ተፅዕኖ ምላሽ ፕሮጀክት በመተግበር ረገድ ባለፉት አምስት ዓመታት ውጤታማ ስራ ማከናወኗ ተገለጸ።
11ኛው የምስራቅ አፍሪካ የስደተኞች ተፅዕኖ ምላሽ ፕሮጀክት ስትሪንግ ኮሚቴ በጋምቤላ ከተማ ሲያካሄድ የቆየው ስብሰባ ዛሬ ተጠናቋል።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ተወካይና በኢጋድ የፕሮጀክቱ የተፈናቃዮች ተፅዕኖ ምላሽ ልማት አስተባበሪ ዶክተር ሙሀመድ ኢልዱማ ፤ ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ በቆየባቸው ባለፈው አምስት ዓመት የተከናወኑት ስራዎች በመሰረተ ልማት፣ በአነስተኛ መስኖ፣ በአካባቢ ደን ልማትና ጥበቃ፣ በማህበረሰብ የኑሮ ማሻሻያና ሌሎች ዘርፎች ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ፕሮጀክትን በመተግበር ረገድ ውጤታማ ስራዎችን ማከናወኗን በመስክ ምልከታ ማረጋገጥ መቻላቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይ በሚተገበረው ሁለተኛ ምዕራፍ የስደተኞች ተፅዕኖ ምላሽ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ በተሻለ አቅምና ስኬት እንደምትፈጽም እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ባስተናገደችው 11ኛው የምስራቅ አፍሪካ የስደተኞች ተፅዕኖ ምላሽ ፕሮጀክት ስትሪንግ ኮሚቴ ስብሰባም የቀጠናው ሀገራት የተሻለ ተሞክሮና መለዋወጣቸውን ጠቁመዋል።
ኢጋድ በቀጠናው በመተግበር ላይ ላለው ለዚሁ ፕሮጀክት ስኬት የክትትልና የማስተባበር ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ዶክተር ሙሀመድ አስታውቀዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የስደተኞች ተፅዕኖ ምላሽ ፕሮጀክት ብሄራዊ አስተባባሪ አቶ ንጋቱ ቦጋለ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ፕሮጀክቱ ሲተገበር የቆየው ስደተኞች በተጠለሉባቸው አምስት ክልሎች ነው ብለዋል።
በክልሎቹ 16 ወረዳዎች በፕሮጀክቱ በተከናወኑ የልማት ስራዎች ከ720 በላይ የትምህርት፣ የጤና፣ የመንገድ፣ የግብርናና ሌሎች የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ተገንብተው ከአንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን በላይ ህዝብ ተጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም በሁለተኛው የፕሮጀክቱ የትግበራ ምዕራፍም በ180 ሚሊዮን ዶላር በ30 የወረዳዎችና በ25 የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች የፕሮጀክቱን ተደራሽነት በማስፋት የአካባቢውን ማህበረሰብና ስደተኞችን ተጠቃሚ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።
የጋምቤላ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ኃላፊ አቶ አጃክ ኡቻላ፤ ባለፉት ዓመታት በፕሮጀክቱ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑት ስራዎች በመስኖና ሌሎች ዘርፎች ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል።
በፕሮጀክቱ በተገነቡት ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች የተማሪ ክፍል ጥምርታውን በማሻሻል የተሻለ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር አስችሏል ያሉት ደግሞ በክልሉ የአቦል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ወይዘሮ ኮከብነሽ ኮረማ ናቸው።
በጋምቤላ ከተማ ሲካሄድ በቆየው የምስራቅ አፍሪካ ተፅዕኖ ምላሽ ፕሮጀክት ስትሪንግ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ የኢጋድ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የኢትዮጵያ ፣የኬንያ፣ የኡጋንዳ ፣የሱማሊያና የጅቡቲ ተወካዮች ተሳታፊ ናቸው።