ቀጥታ፡

ስዊድን በኢትዮጵያ በድርቅና በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች መልሶ ለማቋቋም የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 7/2015 ስዊድን በኢትዮጵያ በድርቅና በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች መልሶ ለማቋቋም የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል በኢትዮጵያ የስዊድን አምባሳደር ሀንስ ሄንሪክ ላንድኩውስት ገለጹ።

ስዊድን በሰሜኑ ጦርነት በትግራይ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ጉዳት ያጋጠማቸው ዜጎችን መልሶ በማቋቋም ሂደት ድጋፍ እያደረገች መሆኑን ገልጸው ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በተመሳሳይ በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎችም በድርቅና ተያያዥ ጉዳዮች ጉዳት ላጋጠማቸው ዜጎች የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ነው የገለጹት።   

ስዊድን በኢትዮጵያ የሚካሄዱ የልማት ሥራዎች በአግባቡ ለመደገፍ የሚያስችላትን ስትራቴጂ መቅረጿንም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በአውሮፓ ኅብረት በኩል ኢትዮጵያን ለመደገፍ በሚደረገው ጥረት ስዊድን የበኩሏን ሚና እየተወጣች እንደምትገኝ ተናግረዋል።

በመንግሥትና በሕወሓት መካከል የተደረሰው የሠላም ሥምምነት በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ለማቅረብ አዎንታዊ ሚና እንደሚጫዎትም ተናግረዋል።

ለበርካታ ዓመታት የዘለቀው የስዊድንና የኢትዮጵያ ግንኙነት አሁን ላይ በተለያዩ የልማት ትብብር መስኮች ላይ እየተጠናከረ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም