ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በምርምርና መማር ማስተማር ልቆ ለመውጣት ዓለም አቀፍ ትስስር ፈጥሮ እየሰራ ነው-ዶክተር ፍሬው ተገኘ - ኢዜአ አማርኛ
ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በምርምርና መማር ማስተማር ልቆ ለመውጣት ዓለም አቀፍ ትስስር ፈጥሮ እየሰራ ነው-ዶክተር ፍሬው ተገኘ
ባህር ዳር (ኢዜአ) ታህሳስ 7/2015 የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በምርምርና መማር ማስተማር ልቆ ለመውጣት ዓለም አቀፍ ትስስር ፈጥሮ እየሰራ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ ገለፁ።
ከባህር ዳር እስከ ደብረማርቆስ ኮሪደር በ122 ሺህ ዶላር የሚተገበርና የተመረቁ ወጣት ሴቶችን ወደ ሥራ የሚያስገባ ፕሮጀክት ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ይፋ ሆኗል።
ፕሬዚዳንቱ በእዚህ ወቅት እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማርና በምርምር ዘርፍ የያዘውን ግብ ለማሳካት ከውጭና ከአገር ውስጥ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በርካታ ፕሮጀክቶችን በትብብር እየተገበረ ይገኛል።
ዛሬ ይፋ የተደረገው ፕሮጀክትም ከእንጅባራ፣ ደብረማርቆስ እና ከአሜሪካው ኢንዲያና ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የሚተገበር መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ ከዩኒቨርሲቲና ኮሌጆች የተመረቁ ወጣት ሴቶችን አቅም በመገንባት ወደ ሥራ ማስገባት የሚያስችል ነው።
"ፕሮጀክቱ ለሴቶች የሥራ እድል ከመፍጠር ባሻገር የተመራማሪዎችን አቅም በመገንባት፣ ዓለም አቀፍ ልምድ በማስገኘት እና ትስስር በመፍጠር ዩኒቨርሲቲው የተቋቋመበትን ዓላማ በላቀ ለማሳካት ያስችላል" ሲሉም አክለዋል።
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ታፈረ መላኩ በበኩላቸው፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ወጣቶችን ተጠቃሚ ያደረገ መሰል ፕሮጀክት መተግበሩን አስታውሰዋል።
"በእዚህም በባህር ዳር እና ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲዎች የልህቀት ማዕከል በማደራጀት ሥራ ፈጣሪዎችን በስልጠና አብቅቶ ወደ ሥራ ማስገባት ተችሏል" ብልዋል።
በፕሮጀክቱ ስልጠና ያገኙ 98 ሥራ ፈጣሪ ወጣቶችን በማወዳደር ለ12 ወጣቶች 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሥራ ማስጀመሪያ ገንዘብ ተሰጥቶ ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉንም አስታውሰዋል።
ዛሬ ይፋ በተደረገው ፕሮጀክትም ምሩቃን ሴቶች ያላቸውን የፕሮጀክት ሀሳብ በማወዳደር በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለ100 ወጣት ሴቶች በልህቀት ማዕከል ስልጠና ሰጥቶ ወደ ሥራ ለማስገባት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ከአሜሪካው ኢንዲያና ዩኒቨርሲቲ የመጡት ዶክተር ተሾመ ይዘንጋው በበኩላቸው የባህር ዳር-ደብረ ማርቆስ ኮሪደር ትስስር የሥራ ፈጠራ ሀሳብ ያላቸውን ሴቶችን ከድህነት ለማላቀቅ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው።
ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚካሄድ ገልጸው፣ "የፕሮጀከት ሃሳብ ያላቸውን ሴቶች አሰልጥኖ ወደ ሥራ የማስገባት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት" ብለዋል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ረዳት የባህል ጉዳዮች መኮንን ሚስተር ስቴዋርት ዴቭስ እንዳሉት የኢትዮጵያ መንግስት ለትምህርት ዘርፉ የሚያፈሰው ሃብት በአፍሪካ ግንባር ቀደም ያደርገዋል።
ኤምባሲው በዜጎች የሥራ እድል ፈጠራ፣ በአቅም ግንባታ፣ በእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዩኒቨርሲቲዎቹን ከአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በማስተሳሰር በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት የባህር ዳርና ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲዎች ከአሜሪካ ሁለት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በሥራ እድል ፈጠራ ለተገበሩት ፕሮጀክት ግማሽ ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጓል ብለዋል።
ዛሬ ይፋ ለተደረገው ፕሮጀክትም ኤምባሲው 122 ሺህ ዶላር በጀት ይዞ ወደ ሥራ መገባቱን ነው የተናገሩት።
በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ መርሃግብር ላይ የዩኒቨርሲቲ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።