መከላከያ የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫን ወሰደ - ኢዜአ አማርኛ
መከላከያ የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫን ወሰደ
አዲስ አበባ መስከረም 19/2011 የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ የ2010 የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ የእግር ኳስ ዋንጫ አሸናፊ ሆነ። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እግር ኳስ የክለቦች የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ጨዋታ ዛሬ በቅዱስ ጊዮርጊስና መከላከያ መካከል ነው የተደረገው። ክለቦቹ በመደበኛው 90 ደቂቃ ያለምንም ግብ አቻ በመውጣታቸው በተሰጠው የመለያ ምት መከላከያ አሸንፎ ዋንጫውን አንስቷል። መከላከያ የኢትዮጵያን የፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች ወክሎ በአፍሪካ መድረክ በኮንፌዴሬሽን ካፕ የሚካፈል ይሆናል። የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ የጥሎ ማለፉ ዋንጫ መካሄድ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ለ14ኛ፣ በአዲስ መልክ ከተደራጀበትና ውድድሩ መካሄድ ከጀመረበት 1990 ዓ.ም ወዲህ ደግሞ ለአራተኛ ጊዜ የዋንጫው አሸናፊ ለመሆን ችሏል። ቅዱስ ጊዮርጊስ የጥሎ ማለፍ ዋንጫውን 12 ጊዜ በማንሳት ሁለተኛው ክለብ ሲሆን የዛሬውን ዋንጫ ቢያሸንፍ ኖሮ ከመከላከያ እኩል በመሆን ክብረ ወሰኑን ይጋራ ነበር።