ቀጥታ፡

የሠላም ሥምምነቱን ተከትሎ ወደ ትግራይ ክልል 229 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የሕክምና ቁሳቁስ ተሰራጭቷል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 7 ቀን 2015 የሠላም ሥምምነቱን ተከትሎ ወደ ትግራይ ክልል ግምታቸው 229 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የህክምና ቁሳቁስ መሰራጨቱን የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ገለጸ።

አገልግሎቱ በመቀሌና በሽሬ የሚገኙ ቅርንጫፍ ቢሮዎቹ በከፊል ሥራ መጀመራቸውንም አስታውቋል።

የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ ለኢዜአ እንዳሉት የሰላም ሥምምነቱን ተከትሎ በሦስት አቅጣጫዎች መድሃኒቶችን ወደ ትግራይ እየተሰራጩ መሆኑን ገልጸዋል።

በመጀመሪያው ዙር 229 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የህክምና ግብዓቶች ወደ ትግራይ ክልል መላካቸውን ጠቁመዋል።

በመቀሌ እንዲሁም በሽሬ የሚገኙ የአገልግሎቱ ቅርንጫፍ ቢሮዎች በከፊል ሥራ መጀመራቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

የመድሃኒቶቹ ዓይነትም የጤና ፕሮግራም መድሃኒቶች (የኤች አይ ቪ/ኤድስ፣ የወባ እንዲሁም የእናቶችና ህጻናት መድሃኒቶች) መሆናቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።

ለመደበኛ፣ ለሕይወት አድን የሚውሉ መሰረታዊ መድሃኒቶችና ለህክምና አገልግሎትና ለላቦራቶሪ ግብዓት የሚውሉ ኬሚካሎች መሰራጨታቸውን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

እንደ ስኳርና ደም ግፊት የመሳሰሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለማከም የሚያገለግሉ መድሃኒቶች መካተታቸውንም አመልክተዋል።

የሁለተኛ ዙር የመድሃኒት ሥርጭት በቀጣዮቹ ቀናት እንደሚጀመር በማከለ።

እንዲሁም የመቀሌና የሽሬ ቅርንጫፎች ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ እንዲገቡ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

መድሃኒቶቹን በማጓጓዝ ወቅት ቅዝቃዜ የሚፈልጉ መድሃኒቶች ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲጓጓዙ መደረጉን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም