የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ትክክለኛ መረጃን በወቅቱ ተደራሽ በማድረግ የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን መከላከል አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ትክክለኛ መረጃን በወቅቱ ተደራሽ በማድረግ የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን መከላከል አለባቸው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 7 ቀን 2015 የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ትክክለኛ መረጃን በወቅቱ ተደራሽ በማድረግ የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን መከላከል እንዳለባቸው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሃመድ እድሪስ አስገነዘቡ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከተለያዩ የፌዴራል ተቋማት ለተውጣጡ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች ለአንድ ወር ሲሰጠው የቆየውን ስልጠና አጠናቋል፡፡
በስልጠናው ከዘጠኝ የፌዴራል ተቋማት የመጡ ከ30 በላይ ባለሙያዎች መሳተፋቸውም ነው የተገለጸው፡፡
ስልጠናው በዋናነት የመልዕክት ቀረጻና ንግግር ጽሁፍ፣ የሃተታ ጽሁፍ፣ የመጽሄት ጽሁፍ አዘገጃጀት፣ ምስልና ድምጽ ቀረጻ እና ሌሎች ተያያዥ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡
በስልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሃመድ እድሪስ፤ ከዲጂታል ቴክኖሎጂ መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሃሰተኛ መረጃ ስርጭት እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
ከትክክለኝነት ይልቅ መረጃን ያለምንም ማጣራት ቀድሞ ለማሰራጨት የሚሰሩ አካላት መበራከታቸውን ጠቅሰው፤ ይህን በተለመደው የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ስራ መከላከል እንደማይቻል አብራርተዋል፡፡
በመሆኑም የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ይህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ትክክለኛ መረጃን በፍጥነት ተደራሽ በማድረግ የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን መከላከል አለባቸው ብለዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ስልጠናው የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች አቅም በማጎልበት ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ለግጭት መስፋፋት ምክንያት እየሆኑ ያሉ መረጃዎችን ማጥራት የምንችለው ብቁ ባለሙያዎችን ስንፈጥር ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ኢዜአ መረጃን ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር ብቁ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን ለመፍጠር እያከናወነ ያለውን ስራ አድንቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው፤ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች በመልዕክት ቀረጻ ወቅት የመረጃ መዛባት እንዳይፈጠር ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ከመልዕክት ቀረጻ በተጨማሪ የመረጃ ተደራሽነት ላይም ትኩረት መስጠት እንዳለባቸውም እንዲሁ፡፡
ከዚህ አኳያ ስልጠናው በዋናነት ወቅቱን በሚመጥን መልኩ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚከናወነውን የኮሙዩኒኬሽን ስራ ለማገዝ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ አስቴር ተክሌና አቶ አበበ ጥላሁን በስልጠናው ለቀጣይ ስራዎቻቸው የሚሆን ሙያዊ አቅም እንዳገኙ ተናግረዋል፡፡
በስልጠናው ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ለሙያ አጋሮቻቸው ለማካፈል ዝግጁ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት፡፡