ቅመማ ቅመም በኩታገጠም የማምረት ዘዴ እየተስፋፋ መምጣቱ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ እንዲጨምር አድረጓል--ባለስልጣኑ - ኢዜአ አማርኛ
ቅመማ ቅመም በኩታገጠም የማምረት ዘዴ እየተስፋፋ መምጣቱ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ እንዲጨምር አድረጓል--ባለስልጣኑ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 7/2015 ቅመማ ቅመምን በኩታገጠም የማምረት ዘዴ እየተስፋፋ መምጣቱ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ እንዲጨምር ማድረጉን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ገለጸ።
የባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በተበጣጠሰ መልኩ ሲከናወን የቆየው የቅመማ ቅመም ምርት ከዘርፉ የሚፈለገውን ያህል ገቢ እንዳይገኝ አድርጎት ቆይቷል፡፡
በተለይ ለግብርና ኤክስቴንሽን ተደራሽነት እንቅፋት በመፍጠር በምርት መጠንና ጥራት ላይ ክፍተት ፈጥሮ ቆይቷል ነው ያሉት፡፡
ከሰብል ልማት ባሻገር ቅመማ ቅመም በኩታገጠም በማለማት ምርትና ምርታማነትን መጨመር እንደሚቻል ገልጸው፤ አሁናዊ የክላስተር ጅምሮችም ውጤታማ እንደሆኑ ገልጸዋል።
ይህም በዘርፉ ያለውን ሃብትና እውቀት በአግባቡ በመጠቀም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚገኘው ገቢ እንዲጨምር ማድረጉን አንስተዋል፡፡
አሁን ላይ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ለመላክ 16 የቅመማ ቅመም ምርቶችን መለየቷን ገልፀው፤ ለዚህም የውጭ ገበያ ግብይት አሰራር ሰርዓት መዘርጋቱን ነው ያወሱት።
ባለፈው የ2014 ምርት ዘመን 14 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ታቅዶ 17 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱንም ነው የተናገሩት፡፡
በተያዘው የ2015 ምርት ዘመን 20 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ለማግግኘት መታቀዱን ጠቅሰው፤ እቅዱን ለማሳካት የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡