ከ4 ኪሎ በላይ አደንዛዥ ዕጽ ይዞ የተገኘው ናይጄሪያዊ በ10 ዓመት ፅኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጣ - ኢዜአ አማርኛ
ከ4 ኪሎ በላይ አደንዛዥ ዕጽ ይዞ የተገኘው ናይጄሪያዊ በ10 ዓመት ፅኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጣ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 7/2015 ከ4 ኪሎ በላይ አደንዛዥ ዕጽ ይዞ የተገኘው ናይጄሪያዊ በ10 ዓመት ፅኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጣ።
ኮኬይን የተባለውን አደገኛ እፅ ይዞ የተገኘው ናይጄሪያዊ በፅኑ እስራት እና በገንዘብ መቀጮ መቀጣቱን የፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ፒተር ኢመሀን የተባለው ናይጄሪያዊ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ተጠቅሞ ከብራዚል ወደ ናይጄሪያ ለመሄድ ሲሞክር በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በተደረገ ፍተሻ መያዙን ገልጿል።
ግለሰቡ በተደረገው ፍተሻ 4 ነጥብ 35 ኪሎ ግራም የሚመዝን ኮኬይን የተባለ አደገኛ እፅ በወገቡ ላይ በማሰር ከኢትዮጵያ ሊወጣ ሲል መያዙንም አስታውቋል።
ሰዎችን ሱስ በማስያዝ ለተለያዩ ወንጀል ድርጊቶች መንስኤ እንዲሆኑ ስለሚገፋፋ እንዳይመረት፣ እንዳይዘዋወር፣ በጥቅም ላይ እንዳይውል የታገደውን የኮኬይን እፅ ፍቃድ ሳይኖረው ይዞ በመጓዝ ላይ የተገኘ በመሆኑ በፈፀመው አደገኛ እፆችን በማዘዋወር ወንጀል ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶበታል፡፡
ተከሳሽ ክሱ ተነቦለት የወንጀል ድርጊቱን ፈፅሜያለሁ ብሎ ያመነ ሲሆን፤ ዐቃቤ ህግ በ10 ዓመት ፅኑ እስራት እና በ20 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ መወሰኑን ከፍትህ ሚኒስቴር የገኘነው መረጃ ያመለክታል።