ቀጥታ፡

የሠላም ሥምምነቱ ለቀጠናው ሠላምና መረጋጋት ትልቅ ሚና ይጫወታል - ኢጋድ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 7/2015 በመንግሥትና በሕወሓት መካከል የተደረሰው የሠላም ሥምምነት በምስራቅ አፍሪካ ሠላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወት የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ገለጸ።

በኢጋድ የሰላምና ጸጥታ ዘርፍ ዳይሬክተር ሲራጅ ፈጌሳ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ለቀጠናው ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ተቀባይነትና ተጽዕኖ ፈጣሪ አገራት መካከል አንዷ መሆኗን አንስተው የአገሪቱ የውስጥ ሰላም ለቀጣናውም ሰላም አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚህ አንጻር በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል የተከሰተውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተደረሰው የሠላም ሥምምነት ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ ነው ያስረዱት።  

ሥምምነቱ በአፍሪካ ኅብረት፣ በኢጋድና በአፍሪካውያን ነባር አመራሮች መሪነት መካሄዱ "ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ" መርህ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

ያም ሆኖ የሠላም ሥምምነቱን ተግባራዊ በማድረግ በምስራቅ አፍሪካ ጠንካራና ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሁሉንም ርብርብ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

ኢጋድም የሠላም ሥምምነቱ ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

በመሰረተ ልማት፣ ንግድና ሌሎች ዘርፎች ቀጠናዊ የምጣኔ ሃብታዊ ትስስርን ለመፍጠር የተጀመረውን ጥረት በማጠናከር በኩልም ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

ኢጋድም የተረጋጋ ቀጠናን ለመፍጠር የአቅም ግንባታ፣ የመረጃ ልውውጥ፣ ግጭትን አስቀድሞ በመከላከል ላይ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ቀጠናዊ ትስስርንና አንድነትን ማጠናከር አገራት የጋራ ሰላማቸው በጋራ እንዲጠብቁ እድል ይፈጥራል።

የኢጋድ ቀጣና ከድርቅ፣ ግጭትና ተያያዥ ችግሮች ጋር ተያይዞ በኅብረተሰብ ላይ የሚደርሱ መፈናቀልና ጉዳት የሚያጋጥምበት አካባቢ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም