ቀጥታ፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት መርሃ-ግብር ዓመታዊ ጉባኤውን በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 7/2015 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት መርሃ-ግብር ዓመታዊ ጉባኤውን በአዲስ አበባ እያካሄደ ይገኛል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ በዚሁ መድረኩ ላይ አጠቃላይ የኢትዮጵያን አሁናዊ የኢኮኖሚና ሁሉን አቀፍ የልማት ስኬቶችና ተግዳሮቶችን አብራርተዋል።

በዚህም መንግሥት የአስር ዓመት መሪ የልማት እቅድ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን፣ በኢንቨስትመንት፣ በኢንዱስትሪ፣ በንግድ፣ በግብርናና ሌሎች የልማት መስክ ሰፊ ስራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።

እ.ኤ.አ በ2019 ተግባራዊ መሆን የጀመረው አካታች አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ተግባራዊ የሆነ እምርታዊ ለወጦችን እያስመዘገበ መሆኑንም ገልጸዋል።

በትምህርት፣ በጤና፣ በአይ ሲ ቲ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍም አገሪቷ ዘርፈ ብዙ ለውጦችን ማስመዝገቧንም አብራርተዋል።

ሂደቱ በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ችግር፣ የኮቪድ 19 ተጽእኖ ሥር የቆየ ቢሆንም በተለይ በኢኮኖሚው ዘርፍ ጠንካራ ሥራዎች መከናወናቸውንም አንስተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተነሳሽነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄም ትልቅ ውጤት እያስመዘገበ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በቀጣይም ኢትዮጵያ የተያያዘችውን የእድገት አቅጣጫ በማስቀጠል አገራዊ የልማት ግቦችን ለማሳካት ትሰራለች ነው ያሉት።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት መርሃ ግብር የኢትዮጵያ ተወካይ ቱሩሃን ሳልህ በበኩላቸው በኢትዮጵያ እየተደረጉ ያሉ የኢኮኖሚና ሁሉን አቀፍ ሪፎርሞች የሚበረታቱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የተባበሩት መግሥታት ድርጅት የልማት መርሃ ግብር ሪፎርሙን በመደገፍ የበኩሉን ሚና ይወጣል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም