ከአርሶ አደሩ ሕይወት መለወጥ ባሻገር በውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ አፈጻጸሙ እያደገ የመጣው የሮዝመሪ ምርት

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 7/2015  የሮዝመሪ ምርት ከአርሶ አደሩ ሕይወት መለወጥ ባሻገር በውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ አፈጻጸሙ እያደገ መምጣቱ ተገልጿል።

በተለምዶ ''የስጋ መጥበሻ'' የሚሰኘው የጥብስ ቅጠል ወይም ሮዝመሪ አይነተ ብዙ የጤና ጥቅሞች እንዳለው በባለሙያዎች የሚነገርለት ተክል ነው።

ከአነስተኛ ጓሮ እንጂ በማሳ ላይ በስፋት ያልተለመደው ሮዝመሪ፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በስፋት ማሳ እየተመረተ፣ የአርሶ ደሩን ሕይወት እየለወጠ፤ ምርቱም ከአገር ውስጥ ገበያ አልፎ ወደ ውጭ እየቀረበ የውጭ ምንዛሪ ግኝት እያስገኘ መጥቷል።

ከሮዝመሪ አምራች አካባቢዎች አንዱ በደቡብ ክልል ስልጤ ዞን ሲሆን፤ በዞኑ ባለፈው በጀት ዓመት ከተመረተው የሮዝመሪ ምርት ከ700 ሺህ ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ተገኝቷል።

በወራቤ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ከይር ሁሴን  ሮዝሜሪን ጓሮ ከመትክል አልፈው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፋት በማምረት ኑሯቸውን እየለወጡ ስለመሆኑ ይገልጻሉ።

አንድ ሮዝሜሪን ተክል እስከ ሰባት ዓመት በየዓመቱ ምርት እንደሚሰጥ ገልጸው፤ የተክል ግብዓት የማይፈልግ፣ በእንስሳት የማይበላ፣ በአሲዳማ መሬት ላይ በቀላሉ የሚመረትና የመሬት ለምነትን የሚጨምር ሰብል እንደሆነ ገልጸዋል።

በዘንድሮው የምርት ዘመን ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በኩታ ገጠም ሮዝመሪ ማልማታቸውን የሚናገሩት አቶ ከይር ሁሴን፤ በትንሹ እስከ 100 ሺህ ብር ገቢ ለማግኘት ዕቅድ አላቸው።

ሮዝሜሪ የተሻለ ውጤታማ እንዳደረጋቸው ገልጸው፤ ለወጣቶች ስራ እድል ፈጠራም ጉልህ ሚና እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

የስልጤ ዞን ቡና እና ቅመማ ቅመም መምሪያ ኀላፊ አቶ ቶፊቅ ኑድ በእናቶች ጓሮ ተወስኖ የኖረው ሮዝመሪ፤ በገበያ ትስስር በመፍጠር አርሶ አደሩን ማበረታታት በመቻሉ የምርት ሽፋኑም በከፍተኛ ፍጥነት አድጓል።

ለማሳያነት በ2012 ምርት ዘመን በዞኑ በ560 ሄክታር መሬት ላይ ብቻ የነበረው የሮዝሜሪ ማሳ በ2015 ምርት ዘመን ከሶስት ሺህ ሄክታር በላይ መድረሱን አንስተዋል፡፡

በዓመት የሚገኘው ምርትም ከ8 ሺህ ወደ 31 ሺህ ኩንታል አድጓል ነው ያሉት።

ሮዝሜሪ ወደ ውጭ ገበያ በመቅረቡ፣ አርሶ አደሮች፣ ላኪዎችና አገር ተጠቃሚ ማደረጉን ጠቅሰው፤ በተያዘው የምርት ዘመንም ከ51 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል።

ከዚህም ውስጥ 70 በመቶው ወደ ውጭ የሚላክ መሆኑን ገልጸው፤ የበለጠ ምርትማነትና ጥራትን ለማሳደግ የተሻለ የገበያ ትስስር በመፍጠር አምራቹን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚያሻ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የገበያ ልማትና ቁጥጥር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሻፊ ዑመር ባለፈው የ2014 የምርት ዘመን በስልጤ ዞን ከተመረተው ሮዝመሪ 710 ሺህ ዶላር የውጭ ምንዛሪ መገኘቱን አውስተዋል።

ባለስልጣኑ ዘርፉን ይበልጥ ምርታማነትና የገበያ ተደራሽነት ለማስፋት፤ የግብይት መመሪያ አዘጋጅቶ ወደ ስራ ማስገባቱን ገልፀው፣ አርሶ አደሩንና አገርን ተጠቃሚ ለማድረግ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ በበኩላቸው ሮዝመሪ በኩታገጠም መልማቱ መልከ ብዙ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመው፣ እንደ ስልጤ ዞን ተመሳሳይ ስነ-ምህዳር ባለባቸው አካባቢዎችም የሚኖሩ አርሶ አደሮች ምርቱን ሊያለሙ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም