የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በ1 ሺህ 300 ወረዳዎች የምክክር ተሳታፊዎች ልየታ በቅርቡ ሊያካሂድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በ1 ሺህ 300 ወረዳዎች የምክክር ተሳታፊዎች ልየታ በቅርቡ ሊያካሂድ ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 7/2015 የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በ1 ሺህ 300 ወረዳዎች የምክክር ተሳታፊዎች ልየታና ምዝገባ በቅርቡ እንደሚጀምር የኮሚሽኑ አመራሮች ገለጹ።
የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ወይዘሮ ኂሩት ገብረሥላሴና ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው የምክክር ሂደቱን ቅድመ ዝግጅት በሚመለከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ከተቋቋመ ስምንት ወራት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአሁኑ ወቅት ስለምክክር ሂደቱ፣ ስለተሳታፊዎች ልየታ የሃሳብ ግብዓት የመሰብሰብ ስራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል።
ምክትል ዋና ኮሚሽነር ኂሩት እንዳሉት ኮሚሽኑ አካታችና አሳታፊ ምክክር የማካሄድ ኃላፊነት ስላለበት በየክልሎቹና በከተማ አስተዳደሮች ከባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ግብዓት የመሰብሰብ ስራ በመጠናቀቅ ላይ ነው።
በዚህም ከፊል አዲስ አበባና ከፊል ኦሮሚያ ክልል ላይ ብቻ ባለድርሻ አካላትን አወያይቶ ግብዓት የመሰብሰብ ስራዎች እንደቀሩ ጠቁመው፤ እነዚህም በጥቂት ቀናት ውስጥ ይጠናቀቃሉ ብለዋል።
ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው በበኩላቸው ኢትዮጵያ ሰፊ ህዝብ ያላት አገር እንደመሆኗ ሁሉም ማህበረሰብ በተወካዮቹ በኩል እንደሚሳተፍ ተናግረዋል።
የባለድርሻ አካላትን አስተያየት በመሰብሰብና መተማመን ላይ በመድረስ ምክክር ከተካሄደ ቅቡልነት እንደሚኖረው በመጠቆም።
የኮሚሽኑ አመራሮች አክለውም ሙሉውን የኢትዮጵያ ህዝብ በምክክሩ ለማሳተፍ ስለሚያስቸግር ሁሉም ኢትዮጵያውያን የተወከሉባቸው ተሳታፊዎች መረጣ ይካሄዳል ብለዋል።
የተሳታፊዎች ውክልና እንደየክልሎቹና ማህበረሰቡ ሁኔታ ዝርዝር መስፈርት እንዳለውና ሁሉም ማህበረሰብ እንዲወከል የሚደረግ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በመሆኑም የተሳታፊዎች መረጣ መስፈርት ላይ ባለድርሻዎችን የማወያየትና የግብዓት መሰብሰብ ስራው እየተጠናቀቀ በመሆኑ በቅርቡ በ1 ሺህ 300 ወረዳዎች የተሳታፊዎች ልየታ እንደሚጀመር ጠቅሰዋል።
ምክክሩ በሁሉም ወረዳዎች ስለሚደረግ በልየታው ውስጥ ምንም ዓይነት ችኮላ ሳይኖር በጥንቃቄ ሁሉም ማህበረሰብ እንዲወከል ይደረጋል ነው ያሉት።
አገራዊ ምክክሩ በተያዘለት ጊዜ እንዲካሄድና የሚጠበቅበትን ብሔራዊ መግባባት የመፍጠር ዓላማ እንዲያሳካ ኮሚሽኑ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው ብለዋል።
በመሆኑም ሁሉም ኢትዮጵያውያን የምክክሩ ተጠቃሚና ባለድርሻዎች በመሆናቸው ለስኬቱ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በምክክሩ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል ነው ያሉት የኮሚሽኑ አመራሮች ያለምንም ገደብ ሁሉም ዓይነት ሀሳቦች ውይይት ስለሚደረግባቸው ሁሉም ለዚህ ዝግጅት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ምክክሩ በገለልተኛነት እንደሚካሄድ ያረጋገጡት ኮሚሽነሮቹ ለውይይት አሳላጮችም ጠንካራ ስልጠና እንደሚሰጥ ተናግረዋል።