ቀጥታ፡

ከ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚገነባው የአማራ ህዝብ ሙዚየም ግንባታ ሥራ ተጀመረ

ባህር ዳር (ኢዜአ) ታህሳስ 7/2015 የአማራ ህዝብን ታሪክ፣ ባህል እና ቅርስን አጉልቶ የሚያሳይና ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚደረግበት ''የአማራ ህዝብ ሙዚየም'' ግንባታ ሥራ በባህር ዳር ከተማ ተጀመረ።

በሙዚየሙ ግንባታ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ጣሂር መሀመድ እንደገለፁት፣ የአማራ ክልል ህዝብ የተለያዩ እምቅ የታሪክ፣ የባህልና የቅርስ እሴቶች ባለቤት ነው።

ሙዚየሙን ለመገንባት በ2009 ዓ.ም የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠ ቢሆንም በወቅታዊ፣ በሀገራዊና ሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች የግንባታ ሥራው እስካሁን ድረስ ሳይጀመር መቆየቱን አስታውሰዋል።

ዛሬ የሙዚየሙ ግንባታ የተጀመረው በባህር ዳር ከተማ ዓባይ ማዶ "አየር ጤና አደባባይ" ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በ15 ሺህ 600 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የሙዚየሙ ግንባታ በ4 ዓመታት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃም የቢሮ ሃላፊው አቶ ጣሂር አስታውቀዋል።

"ግንባታው ሲጠናቀቅም በክልሉ የሚገኙ የአማራ ህዝብ ቅርሶች፣ ባህልና ታሪክ በሙዚየሙ ተሰባስበው ለህዝብ እይታ፣ ለጥናትና ምርምር ሥራዎች እንዲውሉ ይደረጋል" ብለዋል።

በክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የሚገነባውን የአማራ ህዝብ ሙዚየም የግንባታ ሥራ በተቋራጭነት የሚያከናውነው የአማራ ሕንፃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ነው።

በግንባታ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሙዐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን ጨምሮ ሌሎች የክልሉና የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም