አሜሪካ ለአፍሪካ አገራት የሰጠችውን የቀረጥ ነፃ ዕድል ኢትዮጵያ ዳግም እንድትጠቀምበት መፍቀድ አለባት--ላውረንስ ፍሪማን

146

አዲስ አበባ (ኢዜአ)ታህሳስ 6/2015 አሜሪካ ለአፍሪካ አገራት የሰጠችውን የቀረጥ ነፃ ዕድል (አጎዋ) ኢትዮጵያ ዳግም እንድትጠቀምበት መፍቀድ አለባት ሲሉ አሜሪካዊው የፖለቲካ ኢኮኖሚ ተንታኝ ላውረንስ ፍሪማን ተናገሩ፡፡

ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የጣሉትን ሁሉን አቀፍ ማዕቀብ በፍጥነት ማንሳት እንዳለባቸውም ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡

አሜሪካዊው  የፖለቲካ ኢኮኖሚ ተንታኝ ላውረንስ ፍሪማን ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች ለኢትዮጵያ የሚያደርጉት ድጋፍ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ በመገንባት ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ላይ መሰረተ-ልማቶችን መልሳ ለመገንባት ከወዳጆቿ ድጋፍ የምትሻበት ወቅት ላይ ትገኛለች ሲሉም ነው አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት፡፡

ይህንን ጥረት ለማሳካት ደግሞ ምዕራባውያን ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ የጣሉትን ሁሉን አቀፍ ማዕቀብ በአስቸኳይ ማንሳት አለባቸው ብለዋል፡፡

በተለይ አሜሪካ ለአፍሪካ አገራት የሰጠችውን የቀረጥ ነፃ ዕድል (አጎዋ) ኢትዮጵያ ዳግም እንድትጠቀምበት መፍቀድ እንዳለባት ነው ያብራሩት፡፡

ውሳኔው በዋናነት ሕዝብን የሚጎዳ በመሆኑ ዳግም ሊስተካከል እንደሚገባም ነው የጠቆሙት፡፡

ኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን እየጣረች ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የአጎዋ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአስቸጋሪ ሁኔታ አገሪቱን የመሩበትን ብልሃትንም አድንቀዋል፡፡

ይህንን ተከትሎ አሜሪካ ለምዕተ-ዓመት የዘለቀውን የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት አጠናክራ ማስቀጠል አለባት ብለዋል፡፡

በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት የተደረሰው የሰላም ስምምነት ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ እንደሚያስፈልግ በተግባር ያሳየ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

የሰላም ስምምነቱ ጦርነቱን በማስቆም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ሚናው የጎላ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ከዚህ አኳያ አሜሪካና ሌሎች አገራት እንዲሁም አጋር ድርጅቶች በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የወደሙ መሰረተ- ልማቶችን  መልሶ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፉ አሳስበዋል፡፡.

መንግሥት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የወደሙ መሰረተ-ልማቶችን ለመገንባት የሚያደርገውን ጥረት ማጠናከሩ የሰላም ስምምነቱ ፍሬያማ እንዲሆን አጋዥ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡  

በተጨማሪ የመልሶ ግንባታ ሥራው ዓለም በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ያለው እምነት እንዲጨምር ያደርጋል ነው ያሉት፡፡

መንግሥት ከመልሶ ግንባታ ሥራዎች በተጓዳኝ ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ የሚያደርጉ ስልቶችን መተግበር እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም