በኢትዮጵያ ለአምራች ዘርፍ ያለውን ምቹ ሁኔታ ጥቅም ላይ ለማዋል በዘርፉ ውጤታማ ፖሊሲና የአሰራር ሥርዓቶች ሊተገበሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ለአምራች ዘርፍ ያለውን ምቹ ሁኔታ ጥቅም ላይ ለማዋል በዘርፉ ውጤታማ ፖሊሲና የአሰራር ሥርዓቶች ሊተገበሩ ይገባል
አዲስ አበባ (ኢዜአ)ታህሳስ 6/2015 በኢትዮጵያ ለአምራች ዘርፍ ያለውን ምቹ ሁኔታ ጥቅም ላይ ለማዋል በዘርፉ ውጤታማ ፖሊሲና የአሰራር ሥርዓቶች ሊተገበሩ እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና ከጃፓን ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (ጃይካ) ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና በአምራች ዘርፍ ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት ተካሂዷል፡፡
መድረኩም በዋናነት በዘርፉ ያሉ ዕድሎችና ተግዳሮቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በዚሁ ወቅት በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ለአምራች ኢንዱስትሪው ተገቢው ትኩረት እንዳልተሰጠው አስታውሰዋል፡፡
በተለይ ዘርፉን የሚመጥን ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ከመተግበር አንጻር ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ያሉትም ፖሊሲዎች በተገቢው መልኩ ወደ ተግባር እንደማይቀየሩ ተናግረዋል፡፡
ይህም ዘርፉ በሚጠበቀው ልክ እንዳያድግ ማነቆ ሆኖ ቆይቷል ነው ያሉት።
ከዚህ አኳያ የፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግና በተገቢው መልኩ በመተግበር በዘርፉ የላቀ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
መድረኩ በዘርፉ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦችን ለማሰባሰብ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሃሰን መሃመድ በበኩላቸው፣ አምራች ዘርፉ ለኢትዮጵያ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በመሆኑም መንግሥት በዘርፉ የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህን ታሳቢ ያደረገ የፖሊሲ ማሻሻያ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሚልኬሳ ጃጋማ፤ ምርታማነትን ማሻሻል የአገራዊ እድገት ቁልፍ ተግባር መሆኑን አንስተዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ሰፊ የሰው ሃብትን ጨምሮ አምራች ዘርፉን ማሻሻል የሚያስችሉ አቅም እንዳላት አንስተው፤ ይህን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ባለድርሻ ተቋማት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በመድረኩም የአምራች ኢንዱስትሪው አሁናዊ የማምረት አቅም 52 በመቶ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይ ይህን ለማሻሻል እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡
የጃፓን ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ(ጃይካ) የኢትዮጵያ ምክትል ተወካይ ሜጉሚ ሂሮሲ፤ ኢትዮጵያ አሁን እያሳየች ያለው ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ እድገት የሚበረታታ መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የውጭና የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን በማጎልበት የኢኮኖሚ እድገት እንድታስመዘግብ ዘርፉን የሚመሩ ተቋማት ዓለም አቀፍ ልምዶችን በማምጣት ሊተገብሩ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡