የነዳጅ ድጎማው ከታለመለት አላማ ውጭ ለሌብነት መጋለጡን፣ ኮንትሮባንድና ብክነትም በስፋት እየተስተዋለበት መሆኑን ጥናት አመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
የነዳጅ ድጎማው ከታለመለት አላማ ውጭ ለሌብነት መጋለጡን፣ ኮንትሮባንድና ብክነትም በስፋት እየተስተዋለበት መሆኑን ጥናት አመለከተ
አዳማ (ኢዜአ ) ታህሳስ 06/2015 የነዳጅ ድጎማው ከታለመለት አላማ ውጭ ለሌብነት መጋለጡን፣ ኮንትሮባንድና ብክነትም በስፋት እየተስተዋለበት መሆኑን በጥናት ማረጋገጡን የኢትዮጵያ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ገለጸ።
የነዳጅ ድጎማ አተገባበርና በአፈፃፀም ሂደት ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን የዳሰሰ የጥናት ውጤት በኢትዮጵያ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ይፋ ሆኗል።
የኢትዮጵያ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ሃይሌ እንደገለፁት የጥናቱ ዓላማ ህብረተሰቡ ከታለመለት የነዳጅ ድጎማ አሰራር ተጠቃሚ መሆኑን ለማረጋገጥና በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመለየትና ቀጣይ የመፍትሔ እርምጃ ለመውሰድ እንዲያመች ነው ብለዋል።
የታለመለት የነዳጅ ድጎማ የመንግስትን ወጪ ለመቀነስ፣ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ፣ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ፣ በነዳጅ ላይ የሚስተዋለውን ኮንትሮባንድ ንግድና ብክነትን ለማስወገድ ያለመ መሆኑንም አስታውሰዋል።
ይሁን እንጂ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ አተገባበር ሰፊ ክፍተቶችና ችግሮች የሚስተዋሉበት መሆኑን ጥናቱ አመልክቷል።
በተለይ የነዳጅ ማደያዎችና ችርቻሪዎች አካባቢ ሌብነትና ህገ ወጥነት እንዲሁም የኮንትሮባንድና ብክነት በስፋት የሚስተዋል መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህም አልፎ ድጎማው ከህብረተሰቡ ይልቅ አሽከርካሪዎች ባልተፈለገ መልኩ እየተጠቀሙበት እንደሆነ ጥናቱ ማመላከቱን ገልጸው ድጎማ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች መደበኛ አገልግሎት መስጠት ትተው በኮንትራት ስራ ላይ መሰማራታቸውንም ተናግረዋል።
የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ሆነው የ90 ብር ታሪፍ እስከ 200 ብር እንዲሁም የ300 ብር ታሪፍ እስከ 600 ብር እያስከፈሉ መሆኑን ጥናቱ አሳይቷል ነው ያሉት።
ለዚህ ደግሞ በትራንስፖርት ስምሪት አካባቢ የተቀናጀ ስምሪትና ቁጥጥር ያለመኖር፣ የንግድና የትራንስፖርት ዘርፉን የሚመሩ የስራ ሃላፊዎችና ሙያተኞች ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ያለመወጣትና ቅንጅታዊ አሰራር ደካማ መሆን ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
ችግሮቹን ለመፍታት የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ አሰራር ማጠናከር፣ ድጎማውን የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎችን በ'ጂፒ ኤስ' ቴክኖሎጂ መቆጣጠር እንደሚገባ ገልጸዋል።
ችግሮቹን በዘላቂነት ለመቅረፍ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ዓላማን መሰረት ያደረገ አሰራርና የፖሊሲ ማዕቀፍ ማዘጋጀት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
አተገባበሩ ወጥና ውጤታማ እንዲሆን ከፌዴራል ጀምሮ ክልሎች፣ የከተማ መስተዳድሮች፣ ዞኖችና ወረዳዎች ጨምሮ አዋጁን በባለቤትነት መፈጸም እንዳለባቸው አመላክተዋል።
የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ በየወሩ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ መንግስት ለነዳጅ ያወጣ የነበረውን ወጪ ማዳን መቻሉ ተገልጿል።